- ኮሚቴው
ፍጹም ውግዘት የሚገባቸውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች ለይቷል - ማኅበረ
ሰላማ፣ ማኅበረ በኵር፣ የምሥራች አገልግሎት፣ አንቀጸ ብርሃን፣ የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር፣
የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት፣ አሸናፊ መኰንን፣ አግዛቸው ተፈራ፣ ጽጌ ስጦታው እና ግርማ በቀለ
ይገኙባቸዋል።
- “ሃይማኖቴ እንደ አባቶቼ ነው” ያሉት የአባ ሰረቀ እና “የቅን ልቦና የመንፈሳዊና
የፈውስ አገልግሎትን ያቋቋምኹት ልጆቼን የማበላቸው ስለተቸገርኹ ነው” ያሉት የ‹ሊቀ ካህናት› ጌታቸው ዶኒ ጉዳይ
ያለውሳኔ ሐሳብ ለምልአተ ጉባኤው ውሳኔ ቀርቧል።
- አባ ጳውሎስ ከጥንተ አብሶ ጋራ በተያያዘ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕና እንዲመሰክሩ ሊጠየቁ ይችላሉ።
- ሊቃውንት
ጉባኤው ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጎለት ያልቀረበው በጋሻው ደሳለኝ ዛሬ ጠዋት የሊቃውንት ጉባኤውን ሰብሳቢ በእጅጋየሁ
በየነ አማላጅነት ሲለማመጥ ታይቷል፤ ሊቃውንት ጉባኤው “በአንድ ወቅት በራስ ቅል ኮረብታ ላይ ኢየሱስና ዲያቢሎስ
ቁማር ተጫወቱ . . . ዲያቢሎስም በጨበጣ ገባ” የሚለውና ሌሎቹም ጥንቃቄ የጎደላቸው ንግግሮቹ ፍጹም ውግዘት
የሚገባቸው እንደኾኑ አመልክቷል።
- የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አመራርና መዋቅር ይሻሻላል፤ በጠቅላላ ጉባኤና በቦርድ ይመራል፤ የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር እንደሚኾኑ ተጠቁሟል።
- የማኅበራት
መመሪያ ረቂቅ ለውይይት ቀርቧል፤ አሁን ባሉበት አኳኋን ከቀጠሉ “ሌላ ሲኖዶስ ይኾናሉ፤ የፖሊቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ
ይኾናሉ፤ በቀኝ ዘመምና ግራ ዘመም አቋም ቤተ ክርስቲያኒቷን ይውጣሉ/ይከፍላሉ” የሚል ስጋት የቀረበባቸው ማኅበራት
ንብረት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ተጠቃልሎ እንዲተዳደር ሐሳብ ቀርቧል፤ የመመሪያውን ረቂቅ
በጥንቃቄ የተመለከቱት የምልአተ ጉባኤው አባላት ጉዳዩ በይደር እንዲታይ አድርገዋል።
የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በግንቦት 8
ቀን 2004 ዓ.ም ስድስተኛ ቀን ውሎው በፕሮቴስታንት ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገላቸው የቤተ
ክርስቲያናችንን ትምህርተ ሃይማኖት ለማፋለስ፣ ሥርዐተ እምነቷን ለመለወጥ፣ አገልጋዩንና ምእመኑን ለመከፋፈል
በቡድንና በድርጅት ኾነው በመንቀሳቀስ ላይ ስለሚገኙት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች
የተዘጋጀውን ሪፖርት አዳምጧል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ በአጀንዳ ተ.ቁ (13) ላይ ስለ ሃይማኖት
ሕጸጽ በተመለከተው ርእሰ ጉዳይ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ ከሊቃውንት ጉባኤ ጋራ በመኾን የቀረቡ
ማስረጃዎችን መርምረው የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርቡ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት ኮሚቴ ሠይሞ
ነበር፡፡
በወቅቱ የኮሚቴው አባላት እንዲኾኑ ተመርጠው የነበሩት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡-
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ እንድርያስና
ብፁዕ አቡነ ያሬድ ነበሩ፡፡ ጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓ.ም ከተሠየመው ከእኒህ የኮሚቴው አባላት መካከል ሦስቱ
(አቡነ ናትናኤል፣ አቡነ ቄርሎስ እና አቡነ እንድርያስ) በተለያየ ምክንያት መቀጠል ስላልቻሉ ቋሚ ሲኖዶሱ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስንና ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስን ተክቷል፡፡
ኮሚቴው
ከሊቃውንት ጉባኤው የቀረበለትና መርምሮ በትናንትናው ዕለት ከቀትር በኋላ በጸሐፊው በኩል ለቅዱስ ሲኖዶስ በንባብ
ያሰማው ሪፖርት ባለ60 ገጽ ሲኾን በዛሬው ዕለት ምልአተ ጉባኤው በሪፖርቱ ላይ በመወያየት የውሳኔ ሐሳቡን ያጸድቃል
ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሪፖርቱ በፕሮቴስንታንት ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገላቸው
ኦርቶዶክሳውያን መስለው በሁሉም የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ እና የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ
በመሰግሰግ ፕሮቴስታንታዊ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ከሚንቀሳቀሱት ማኅበራት መካከል በስምንቱ ላይ ያተኮሩ የኅትመት
ውጤቶችን፣ የድምፅ እና ምስል ማስረጃዎችን መርምሯል፡፡
የፕሮቴስታንት እምነት ተቋማት
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ያላቸውን የመሠረተ እምነት /ዶግማ/ ልዩነት /ድንበር/ አጥፍተው
ቤተ ክርስቲያናችንን በቁጥጥር ሥር አውለው ባለችበት ፕሮቴስታንታዊ ማድረግ ወይም ቤተ ክርስቲያናችንን የጦርነት
ቀጣና በማድረግ እንደ ሕንድ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት መክፈል ዓላማ ያላቸው ማኅበራቱ በአሁኑ ሰዓት በሚያወጧቸው
መጻሕፍትና መጽሔቶች እንዲሁም በራሪ ወረቀቶች የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በግልጽ ይቃወማሉ፤ አገልጋዩና ምእመኑ
በማይመች አካሄድ እንዲጠመድ እና በዘረኝነት እንዲከፋፈል ጭምር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህም በማስረጃ ተደግፎ የቀረበ
በመኾኑ ፍጹም መወገዝ ያለባቸው ማኅበራት ተለይተው ቀርበዋል፡፡
ከእኒህም ውስጥ ኮሚቴው ፍጹም ውግዘት እንዲተላለፍባቸው የውሳኔ ሐሳብ ከቀረበባቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራት መካከል፡-
1. ማኅበረ ሰላማ - በክልል ትግራይ ፍትሕ ቢሮ ተመዝግቦ ፈቃድ ባወጣበት ስሙ
ማኅበረ ሰላማ ምትሕግጋዝ ማኅበር (
Abune Selama Self Help Association) እየተባለ የሚጠራና ዋና ጽ/ቤቱ መቐለ የሚገኝ ነው፡፡ ባወጣው ፈቃድ መሠረት በልማት ሥራ ላይ መሳተፍ ሲገባው ከሕገ ወጥ ባሕታውያንና ሌሎች የተሐድሶ ማኅበራት ጋራ በመቀናጀት
‹‹በገዳማት ላይ ጥናት ማድረግ››
በሚል ሰበብ በቅርሶች ላይ ከፍተኛ ዘመቻ በማካሄድ ማንነትን ለማጥፋትና በአቋራጭ ለመክበር ይንቀሳቀሳል፤
ዘረኝነትን ያስፋፋል፡፡ የአሲራ መቲራው ገዳም አበምኔት ነኝ ባዩ አባ ገብረ መድኅን ገብረ ጊዮርጊስ ከማኅበሩ
መሪዎች ጋራ በድብቅ በመገናኘት ዕቅዱን ለማስፈጸም ይንቀሳቀሳል፡፡
2. ማኅበረ በኵር
- በ1983 ዓ.ም የተመሠረተ ሲኾን መሥራቹ በ1953 ዓ.ም ከቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተባረረው መሠረት
ስብሐት ለአብ ነው፡፡ ከምሥረታው ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በፕሮቴስታንቶች ድጋፍ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሌሎች የተሐድሶ
ኑፋቄ ማኅበራት ‹‹አርኣያችን ነው›› ይሉታል፡፡
‹ጮራ› የተሰኘ
መጽሔት ያሳትማል፡፡ መጽሔቱን በሕገ ወጥ መንገድ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለሰንበት ት/ቤቶችና ለከፍተኛ ትምህርት
ተቋማት ግቢ ግባኤያት ይልካሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት አግዛቸው ተፈራ የተባለው በዋና አዘጋጅነት በሚሠራበት መጽሔት
የጸሎት መጻሕፍትን ይቃወማሉ፤ አባቶችን ይዘልፋሉ፤ አዋልድ መጻሕፍትን አይቀበሉም፤ ‹‹ቅዱሳት ሥዕላት
አያስፈልጉም›› ይላሉ፤ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አሁንም አማላጅ ነው››፤ ሥልጣነ ክህነትን አይቀበሉም፤ የእምነት
ልዩነት ድንበርን ያፈርሳሉ፤ ‹‹ቅዱስ ቍርባን መታሰቢያ ነው፤ ውላጤ ኅብስት የለም›› ይላሉ፤ ምስጢረ ሜሮንን
ይቃወማሉ፤ ‹‹ሥጋ በተዋሕዶ የባሕርይ አምላክ አልኾነም›› ይላሉ፡፡
3. የምሥራች አገልግሎት - በ1990 ዓ.ም የተመሠረተና አሸናፊ ሲሳይ በተባለ ግለሰብ የሚመራ ሲኾን
‹‹ቤተ ክርስቲያን የውጊያ ቀጣና ናት›› በማለት
ለእንቅስቃሴው የሚረዱ 34,000 ‹‹እርሾዎችን›› በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለመሰግሰግ ከፍተኛ የገንዘብና
የማቴሪያል ድጋፍ የሚደረግለት፣ እያንዳንዳቸው ከ100 - 160 አባላት ባሉት ኅቡእ ቡድን (
Cell based) የሚንቀሳቀስ አካል ነው፡፡
‹‹ፕሮቴስታንት እና ኦርቶዶክሳውያን በመሠረተ እምነት አንድ ናቸው›› ከሣቴ ብርሃን ከተባለው ድርጅት ጋራ አንድ ዐይነት ዓላማ ያራምዳል፤ የክርስቶስን አምላክነት በአግባቡ አያምንም፤ ምንኵስናን ይቃወማል፤ አዋልድ መጻሕፍትን አይቀበልም፡፡
4. አንቀጸ ብርሃን -
ከሰበታ መካነ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት ተለይቶ የወጣው አሸናፊ መኰንን
የሚያሳትማቸውን የኑፋቄ መጻሕፍት ያስተዋውቃል፡፡ በሌላ ስያሜው ራሱን ‹‹ማኅበረ መንፈስ ቅዱስ›› እያለ
ይጠራል፡፡
‹‹የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን እምነትና ሥርዐት የጠበቀ መንፈሳዊ ጽሑፍ›› በሚል በኅቡእ በሚያሰራጫቸው ጽሑፎቹ ምሥጢረ ሥላሴን አፋልሶ ያስተምራል፤ ምስጢረ ሥጋዌን በማፋለስ ቅብዐትን ይሰብካል፤ በካህን ፊት የሚደረግ ኑዛዜን ይቃወማል፡፡
5. የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር
- በኑፋቄያቸው ከማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተክለ ሳዊሮስ ሰንበት ት/ቤት የተሰናበቱ ተወግዞ
የተባረረው የሃይማኖተ አበው ማኅበር ሰለባዎች ነው፡፡ አቶ መስፍን በተባለ ግለሰብ ይመራል፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ወደ
ፕሮቴስታንትነት መቀየራቸውን ሳያውቁት ሃይማኖታቸውን የሚያስክዱ የርቀት ትምህርቶችን ይሰጣል፤ ኅትመቶችን
ያሰራጫል፤ ቤተ ክርስቲያንን በግልጽ ይዘልፋል፤ የሥጋ ወደሙን አማናዊነት አያምንም፡፡
6. የእውነት ቃል አገልግሎት
- ድርጅቱ ይህን ስያሜ ከመያዙ በፊት በመጀመሪያ BGNLJ (Brothers Gathered Unto Lord
Jesus) በኋላም (Bible Truth Ministry) እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የድርጅቱ መሪ በቅዱስ
ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና ማኅበረሰብ ብርታት የተባረረው ግርማ በቀለ ነው፡፡ ሌላው ተጠቃሽ ግለሰብ
ሥዩም ያሚ የሚባለው ነው፡፡ ድርጅቱ ከእንግሊዝኛ በሚተረጉማቸው መጻሕፍት የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ክፉኛ
ያብጠለጥላል፤ በየክልሉ በከፈታቸው ቅርንጫፍ ማከፋፈያዎች ጽሑፎችን በነጻ በማደል፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ታሪክን
በማዛባትና በአዋልድ መጻሕፍት ላይ የማይገባ ትችት በመሰንዘር አገልጋዮችን ያደናግራል፡፡