Tuesday, September 18, 2012

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ዜማውና 1500ኛ አመት መታሰቢያ ክፍል አንድ



ቅዱስ ያሬድ ከአባቱ ከአብዩድ /ይስሐቅ/ ከእናቱ ከክርስቲና /ታውካልያ/ 505 .. ሚያዚያ 5 ቀን በአክሱም  ተወለደ፡፡ በዚህም መሰረት ታላቁ ቅዱስ ያሬድ በሚመጣው ሚያዝያ አምስት 1500 ዓመት ይሆነዋል ማለት ነው ፡፡ ታዲያ የዚህ ታላቅ አባት ለኢትዮጵያ እና ለቤተ ክርስቲያናችን ካበረከተው ታላቅ የአለም ሀብት አንፃር 1500ኛ አመቱ በታላቅ ድምቀት አመቱን ሙሉ መታሰብ ይኖርበታል ፡፡
መቼም ቢሆን እንዲት ሃገር የራሷ የሆነው ባህሏ / ሥርዓቷ/  የሚያኮራትና ማንነቷንም የሚያንጸባርቅ  በመሆኑ ልትጠብቀውና ከትወልድ ወደ ትውልድ ልታስተላልፈው የባለቤትነት ግዴታዋ ነው ፡፡ በመሆኑም ሀገራችን ኢትዮጵያን ለጥቁር ሕዝቦች መኩሪያ እንድትሆን ያደረጋት የልጆቿ ሀገር ወዳድነትና ጀግንነትን የተመላው ባህሏ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት፣ የሥነ ዜማ ሀገር መሆኗም መጻሕፍተ ታሪክን ባነበቡ ሊቃውንት አንደበት ብቻ ሳይሆን በማዳመጥ  ትውፊት /ርክክብ/ ለኅብረተሰቡ ኀቡእ ያልሆነ ነገር መሆኑ ነው ፡፡
በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት ዑደት ስፍር ቀምር የራሷን  ዜማ ያደላደለች አፍሪካዊት እመቤት ናት ብንል ጽልመት ሊጋርደው የማይችለው ገሀድ ነው፡፡ 

ይሁን እንጂ እኛ ልጆቿ የትናንቱን ለዛሬ ትውልድ ማበርከት ያልቻልን ይመስላል ፡፡   ለዚህም ነው ትናንት የተነሱ የዜማ ሊቃውንት እነ ሞዛርት ከቅዱስ ያሬድ 1250 ዓመት ብኋላ የተወለዱት በዓለም የዜማ ሊቃውንት ሲባሉ ቀደምት የሆነው ቅዱስ ያሬድ ግን ኢትዮጵያውያን እንኳን ስራውን እንዳንዘክረው ስራዎቹን ተራ ስራ ተደርገው እንዲታዩ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም፡፡
አበው ለብዙ ዘመናት ይህን ዜማ  በዜማ ቤቱ፣ በቅኔ ቤቱ በመጻሕፍት ቤቱ እንዳልተጠቀሙበት ሁሉ ዛሬ ግን የአበው ያለህ ብለን  ቅዳሴውን በንባብና በአማረኛ ለውጠን ዜማው እነዲዘነጋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረግን ነው፡፡ ይህ ግን “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” ሳያሠኝ አይቀርም ፡፡ 

Friday, September 14, 2012

መስቀልና እመቤታችን

በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ 
  • መግቢያ 
በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ለእያንዳንዱ የቤተሰብእ አባል የራሱ የሆነ ቦታ ወይም ደረጃ አለው፡፡ እናት ያላት ቦታ አለ፡፡ አባት ያለው ቦታ አለ፡፡ ልጆች ያላቸው ቦታ ደግሞ ይኖራል፡፡ የልጆች ቦታ እንኳን እንደ እድሜያቸውም ሆነ እንዳላቸው የትምህርት፣ የሥራና የሥነ ምግባር ሕይወት የተለያየ ነው፡፡ የታላቅ ልጅ ቦታ ከታናሽ ይለያል፡፡ይህ ዓይነቱ የመዋቅር ልዩነት በየትም ቦታ ይታያል፡፡ በወታደር ቤት ይህ ልዩነት አለ፡፡ በቢሮና በማናቸውም መድረክ ይህ ዓይነቱ ልዩነት የተጠበቀ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአንድ ሰው ውስጥም በአካል ብልቶች መካከል ይህ ልዩነት አለ፡፡ ልዩነቱ የኃላፊነት፣ የወሳኝነትና የአስፈላጊነት መጠንን ይገልጣል፡፡ ይህን ልዩነት ተከትሎ የሚመጣ ነገር ደግሞ አለ፡፡ ይኸውም የክብር ልዩነት ነው፡፡
ንዋያተ ቅድሳትም ሁሉ ክብራቸው የተለያየ ነው፡፡ የሥዕል ክብር ከመስቀል፤ የመስቀል ከታቦት የታቦት ከመንበር፤ የመንበር ከአጎበር፤ የመጻሕፍት ከኩስኩስት፤ የጻሕል ከጽዋዕ ወዘተ የተለያየ ነው፡፡  
ወደ ቅዱሳን ምእመናን ስንመጣ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ምእመናን በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ሲኖሩ የራሳቸው የሆነ አሰላለፍ አላቸው፡፡ ይህም በዕድሜና በሌላ ሥጋዊ መመዘኛ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሚዛን ነው፡፡
ቅዱሳን አንዳቸው ከአንዳቸው በመንፈሳዊ ጸጋና ማዕርግ፣ በክብርም የተለያዩ ናቸው፡፡ ወንጌል እንደገለጠችው ባለ ሠላሳ ፍሬ አለ፤ ባለ ስልሣ ፍሬ አለ፤ ባለ መቶ ፍሬ ደግሞ አለ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ይህን የማዕርግ ልዩነት ሲያስረዳ ‹‹በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና፡፡›› ብሏል፡፡ (1ቆሮ15.41) አበው ‹‹ከጣት ጣት ይበልጣል›› እንዲሉ፡፡ ስለ ክብርና ልዩነት ይህን ሁሉ ያተትነው መስቀልና እመቤታችን በክብር እኩል ናቸውን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መንደርደሪያ እንዲሆነን ነው፡፡

ፍሬዋን ለመብላት




መውተርተር መግተርተር ይኑርህ መታታት
መማረክ እጅ መስጠት ትሁን ለጠላት
ለማሸነፍ ይሁን ሁሌም ፆም ፀሎት



ርዕይ የሌለህ እንዳትሆን ከንቱ
ንደፍ ተልዕኮህን አሳውቅ በብርቱ
ይታይሃልን በጭላንጭል ክፍቱ

Sunday, September 9, 2012

አሮጌውን ሰው አስወግዱ ኤፌ. 4:22

በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው 

 "ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ  በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።" ኤፌ4:22-24


"እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ።"ኤፌ4:17

 

" የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።" 1ጴጥ.4:3

Friday, September 7, 2012

ርኅወተ ሰማይ እና ጳጉሜ 3 የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል መታሰቢያ



ርኅወተ ሰማይ በቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩ ታላላቅ በአላት መካከል አንዱ ሲሆን የሚውለውም ጳጉሜ 3 በየዓመቱ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ቀን ነው፡፡ ርኅወተ ሰማይ የስሙ ትርጉም የሰማይ መከፈት እንደማለት ሲሆን በክርስቶስ ክርስቲያን የተባሉ ሁሉ ፀሎት፣ ልመናቸው ምልጃቸው የሚያርግበት ከአምላክም የሚወርድበት አለት ነው፡፡ በዚህች እለት ቅዱሳን መላእክት የምእመናንን ልመና መስዋእቱን የሚያሳርጉበት እና የአምላካችንን ምህረት ቸርነት ለሰው ልጆች የሚያወርዱበት እለት ፡:

በዚህች ቀን በሚዝንመው ዝናምም በእግዚአብሔር ቸርነት ብዙ ድውያን ፈውሰ ሥጋ ፈውሰ ነፍስን ያገኛሉ መካኖች ከማየ ፀሎቱ ጠጥተውም ማህፀናቸው ይከፈታል ሌሎች ብዙ ተዓምራትም ይደረግባታል፡፡
ጳጉሜ 3 የሊቃነ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል  መታሰቢያ ነው ፡፡
ቅዱስ ሩፋኤል የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን (ራጉኤልን ልጅ) ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቃት መሆኑ በመጽሐፈ ጦቢት በስፋት ተገልጿል፡፡
"የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ እፈልጋለሁ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፣ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ› ሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡" መጽ. ጦቢት::
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡

Wednesday, September 5, 2012

ፕሮቴስታንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ንዋያተ ቅድሳት በመዝረፍ ላይ

በቪሲዲ ከተደገፈ መረጃ ጋር 
 ፕሮቴስታንት እምነቱ ይህ ነው ሥርዓቱም ይህ ነው ለማለት አይቻለም ይልቁንም በአብዛኛው የራሳቸው የሆነ ወጥ ሥርዓት የሌላቸው በመሆናቸው ማንነታቸውን በትርጉም በትክክል  ለመግለጥ ሁልጊዜ አስቸጋሪ ሆኖ ይኖራል፡፡ በአብዛኛውም ግሎባላይዜሽን ባመጣው አዳዲስ ኩነቶች እራሳቸውን  በማመሳሰልና ጊዜውን በመምሰል የሚያክላቸው እስካሁን አልተገኘም፡፡
ይሁን እንጂ መቃወም ተቃውሞአዊ ጠባይ የሚያይልባቸው መሆኑን ከአንዳንድ መረጃዎች መረዳት ይቻላል በየጊዜውም የሚነሡት ሁሉ ከእነርሱ በፊት የነበረውን ትምህርት እየተቃወሙ በየጊዜው አዳዲስ ትምህርት እንዲያመጡና ክፍልፋያቸው (Denomination) እንዲበዛ አድርገዋል፡፡
 በዚህ ጊዜ ውስጥ መሠረታዊና እውነተኛ ትምህርተ ሀይማኖት እንዲኖራቸው ከምክንያቶቻችን ይልቅ በመገለጥ  ሃይማኖት አምነው ትምህረተ ሥላሴን እንዲቀበሉ ያደርጉ ሰዎችም እንደ ተነሱ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ በዓለም ላይ ከደረሱትም ጉዳት አንዱ የሰውን  ምግባር (moral) መለወጥና እንስሳዊና ሰይጣናዊ ማድረግ ነው፡፡
 እስካሁንም በነበራቸው አካሄድ እግዚአብሔርን እናመሰግንበታለን የሚሉት መዝሙራቸው ዘመናዊ ዘፈን እንደሆነ የራሳቸው ሰው የተናገረውን እናነሳለን ለእኛ እንደ ኢትዮጵያ ክርስቲያኖች የሚያስፈልገን ሽብሸባ  እንጂ ዳንስ ሊሆን አይገባም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በዓለም ከታወቀችበት ትውፊቶች የራሷ የሆነ አገራዊ ዝማሬ ያላት መሆኑ ነው፡፡ ይህም ብዙዎቻችን የምንወደው ያሬዳዊ ዝማሬ ነው ያሬዳዊ ዝማሬ ለብዙዎቻችን የምንወደው ያሬዳዊ ዝማሬ ለብዙ የኢትዮጵያ ህዝብ ጆሮ የሚሰጠው ምልክት ቀውስ ዳንስ ወይም ጭፈራ ሳይሆን አምልኮ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የበገናን ስንትርትር ዜማ ስንሰማ ልባችን ይቀልጣል እንግዲያው እግዚአብሔር በባህላችን ውስጥ ባስቀመጠው በዚህ መልካም ነገር ተጠቅመን ለማገልግልና ለማነጽ  ብንሞክር መልካም ይመስለኛል፡፡ ቀናነት ካለን!  በማለት ብሶቱን አሰምቷል ዳንሳቸው እያደረሰ ያለውን ጉዳት ቀውስ ብሎ በመጥራት ገልጦታል፡፡  ይህ ግርማዊ የተባለ ፀሐፊ የብልፅግና ወንጌል ብሎ በ1992 ባሳተመው መጸሐፍ ላይ የተገለጸ ሲሆን ዛሬ ላይ ደግሞ ሰሞኑን ባሳተሙት የመዝሙር ካሴቶች ቅዱስ ያሬድን ሊያስተዋውቁን እንዲህ ዳዳቸው፡፡     ለቀባሪው አረዱ እንዲሉ:: ይህን ቪሲዲ ይመልከቱ

Tuesday, September 4, 2012

ቅዱስ ሲኖዶስ የፀሎት ጊዜ አወጀ



ቅዱስ ሲኖዶስ  የፀሎት ጊዜ አወጀ ጊዜያቱም ከጳጉሜን 1/2004 - መስከረም 10/2005 ዓ.ም ድረስ መሆኑ ታውቋል፡፡
ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላም እና አንድነት እንዲኖር አገልግሎቷም የተቃና እንዲሆን ለማድረግ የሱባኤ ጊዜ አስፈላጊ በመሆኑ ለ15 ቀናት ካህናትና ምእመናን በአንድነት እግዚአብሔርን በፀሎት የሚማፀኑበት እንዲሆን ቅዱስ ስኖዶስም ሱባኤውን የተመለከተ መግለጫ  በቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊው በኩል አሳውቋል፡፡
የሱባኤው ጊዜ የታወጃል ከተባለ ሰንበት ቢልም በዛሬው እለት ግን የሱባኤውን ጊዜ ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ መልእክት ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች እንዲዳረስ ያድርጉ ፡፡
አምላካችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ከፈተና ይጠብቅልን፡፡

Monday, September 3, 2012

ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ ነው ምስጢረ ሥላሴንም አስተምሯል

በአካል በስም፣ በግብር ሦስት፣ በመለኮት፣ በባሕርይ በህልውና አንድ ሁኖ አንድ አምላክ እየተባለ ዘለዓለም ሲቀደስ ኑሯል፤ይኖራል፡፡
ሥላሴ በስም:- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ፡፡ በግብር አብ ይወልዳል፤ ያሠርጻል፤ ወልድ፤ ይወለዳል፤ መንፈስ ቅዱስ ይሠርጻል፡፡ በአካል አብም፤ ፍጹም አካል (ህልውና፤ ገጽ) አለው፤ እንደዚሁም ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ የተለየ ፍፁም አካላት አሏቸው። 

አካልና ሰውነትን ባለማወቅ ሰዎች ያደባልቋቸዋል፤ አካል ሦስቱም፣አብ ወልድ ፡ መንፈስ ቅዱስ ለእየራሳቸው አሏቸው ሰውነት ግን የሚጨበጥ የሚዳሰስ ያለው ወልድ ብቻ ነው፡፡ ይኽውም ሥጋ በመልበሱ፡፡ በምስጢረ ሥላሴ አካል ለቀዋሚ ነገር ለመንፈስ ነው የሚነገረው፤ አይታይም አይዳሰስም፤ መንፈስ ነው፡፡ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ በተለየ ረቂቅ አካሉ ስጋ ስለተዋሀደ የሚዳሰስ አካል አለው እንላለን፡፡

ባሕሪያቸው መለኮታቸው፣ መንግሥታቸው፣ ሥልጣናቸው ግን አንድ ነው፡፡ በአካል ሦስት ስለሆኑና በመለኮት፣ በባሕርይ አንድ ስለሆኑ፣ እኔ እያለ በነቢያት በክርስቶስ፣ በሐዋርያት፣ እግዚአብሔር ሲያናግር ኑሯል፡፡

  •   (ዮሐ. 1፡1-3) በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ይህ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ሁሉም በእሱ ሆነ፡፡ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ የሆነ የለም። ከዚህ ላይ ከመጀመሪያ ጀምሮ ከእግዚአብሔር አብ ጋራ ሌላ እግዚአብሔር ወልድ እንዳለ እና ያለእሱም ምንም እንዳልሆነ ይናገራል፤ በአካል የተለያዩ በመለኮት ግን አንድ የሆኑ፤ ሁለት አካላት፤ አንድ እግዚአብሔር እንድ እግዚአብሔር እንዳለ ወንጌላዊው ቁልጭ አድርጎ ገልጧል፤ ከዚህ ላይ የተጠቀሱት ሁለቱ አካላት አብና ወልድ ናቸው፣ ዝቅ ስንል ደግሞ ሦስት አካላት መሆናቸውን እናያለን፡፡
  •   (ማቴ.3፡16-17) ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኋ ወጣ፤ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ወርዶ ከእሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ እነሆም ድምፅ ከሰማይት ወጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ፡፡ በዚህም በአምሰላ ርግብ የወረደው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፤ የምወደው ልጄ ያለ እግዚአብሔር አብ ፤ ተጠማቂው ሰው የሆነው እግዚአብሔር ወልድ በትስብእቱ ዐማኑኤል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለው፣በኋላ የቤተክርስቲያ ሊቃውንት ሥላሴ ብለው የሰየሟቸው አካላት፣ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡(ማር.1፡911፤ ሉቃ.3፡21-22)