(ደቂቀ ናቡቴ መስከረም 24,2005 ዓ.ም ከሐመር መፅሄት የተወሰደ(ዲ.ን
ያረጋል አበጋዝ)) ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን
ኃይለ ቃልን ከትርጓሜ
ትርጓሜን ከምሥጢር እንዲሁም
ደግሞ ምሥጢርን ከዜማ
ጋር አስተባብረውና አስማምተው
የሚደርሱ ሊቃውንት ባለቤት
ናት፡፡
'ብኪ
ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ፣
ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአግሪሁ ለይሁዳ
ጸቃውዐ መዓር ወሀሊብ ፀዓዳ›
ጸቃውዐ መዓር ወሀሊብ ፀዓዳ›
ያለው ይህም ማለት ነቢዩ ኢዩኤል ከይሁዳ ተራሮችና ኮረብቶች ጣፋጭ ማርና ፀዓዳ ወተት ይፈሳል÷ ይመነጫል ያለው በአንቺ ተፈጸመ ማለት ነው፡፡ ይህም እመቤታችን ክርስቶስን በወለደች ዕለት መሪሩ ጥሞ፣ ይቡሱ ለምልሞ ተገኝቷል፡፡ ይህ
ለጊዜው ሲሆን ፍጻሜው ደግሞ ከእርስዋ በነሣው ሥጋና ደም ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ፣ ከልጅነት ተራቁቶ፣ በረሀበ ነፍስና በጽምዓ ነፍስ ተይዞ የነበረውን የሰው ልጅ ከጐኑ ውኃን ለጥምቀት፣ ሥጋውንና ደሙን ምግበ ነፍስ አድርጎ የአምስት ሺህ
አምስት መቶውን ዘመነ ረሀብ እንዳስወገደልን ያስረዳል፡፡
አርምሞትኪ ማርያም ኃለፈ እምአንክሮ
እስከ ንሬኢ ሕዝብኪ ለተአምርኪ ግብሮ
ገነትኪ ትጽጊ ሰላመ ወተፋቅሮ
እለ ያማስኑ ለዓፀደ ወይንነ ወፍሮ
ናጽለ ንዑሳነ አፍጥኒ አሥግሮ
ትርጉም
‹‹እመቤታችን ማርያም ሆይ አርምሞሽ ከማድነቅ በላይ ሆነ÷
በማድነቅ የማይፈጸም ሆነ፡፡ … የወይን ቦታችንን የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮዎች ለማጥመድ (ለመያዝ) ፍጠኚ፡፡›
ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ነገሩን ሁሉ
በልቧ ትጠብቀው ነበር›› (ሉቃ.2÷51) ሲል
የእመቤታችን አርምሞ እንዴት አስደናቂ እንደሆነ ገልጿል፡፡ እመቤታችን ማንም ፍጡር ያልሰማውን ብሥራተ መልአክ የሰማች÷ ለማንም ያልተደረገውን በድንግልና መጽነስና መውለድ የታደለች÷ ማኅፀኗን ዓለም አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲመሰገንባት የመላእክትን ቅዳሴ የሰማች ፈጣሪዋን የመገበች፣ ከሰው ወገን ይቅርና ከሱራፌልና ከኪሩቤል የሚበልጥ ክብርና ጸጋ የታደለች ስትሆን እርሷ ግን በዚህ ዓለም ስትኖር ሁሉንም ነገር በልቧ ከማኖር በስተቀር ይህንን አየሁ÷ ይህንን ሰማሁ አላለችም፡፡ ሔዋን ዕፀ በለስን ወደ መብላትና ጸጋዋን ወደማጣት ያደረሳት ለእርስዋና ለአዳም ብቻ የተነገረውን ምሥጢር አውጥታ ለዲያብሎስ በመናገርዋ ነበር፡፡ እመቤታችን ግን
ሁሉን በልቧ መዝገብ በመያዟ የተመሰገነች ሆነች፡፡
ከክርስቶስም ሆነ
ከእመቤታችን የተማርነው አርምሞን ነው፡፡ ክርስቶስን ጲላጦስና ሊቃነ ካህናቱ ከየት መጣህ? ማነህ? ትምህርትህስ ምንድነው? እያሉ ሲጠይቁት ዝም
ነው ያላቸው፡፡ ልሰቅልህ ሥልጣን አለኝ ሲለው ብቻ ነው መልስ የመለሰለት፡፡ ስለዚህ እኛም ከአባታችን ከክርስቶስና ከእናታችን ከድንግል ማርያም ያየነውን አብነት ማንሣት ይገባናል (ዮሐ.19÷2፣
ማቴ.27÷14)፡፡
የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ የእመቤታችንን አርምሞ ከአደነቀ በኋላ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹እሥግሩ ለነ
ቈናጽለ ንዑሳነ እለ
ያማስኑ ዓፀደ ወይንነ - የወይናችንን ቦታ
የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን›› (መኃ.2÷15) እንዳለ የወይን ቦታ የተባለ የሕግ መጠበቂያ ልባችንን ሊያበላሹ ውር ውር
የሚሉትን በቀበሮ የተመሰሉ መናፍቃንንና አጋንንትን እንድታስታግስልንና እንድታስወግድልን ይጸልያሉ፡፡
ትመስል እምኪ ማርያም ዕለተ ሣልስተ ወራብዕተ
ዘወለደት ጽጌ ወፀሐየ ዓለም ብርህተ
ካዕበ ትመስል ሳብእተ ዕለተ
እስመ ፈረየት ኪያኪ ተአምረ ግዕዛን ሰንበተ
ለእለ በሰማይ ወምድር ዘከንኪ ዕረፍተ፡፡
‹‹ማርያም ሆይ እናትሽ (ሐና)
ጽጌያት የተፈጠሩባትን ሦስተኛዋን ቀን፣ ፀሐይ የተፈጠረችበትን አራተኛውን ቀን
(ረቡዕ)፣ እንዲሁም እግዚአብሔር ሥራውን የፈጸመባትንና ያረፈባትን ሰባተኛዋን ቀን
ትመስላለች፡፡ ምክንያቱም በሰማይና በምድር ላሉ
ሁሉ ዕረፍት የሆንሻቸውን አንቺን ወልዳለችና፡፡››