Thursday, October 4, 2012

ማኅሌተ ጽጌ፡- ምንጩ - ትርጉሙ - መልእክቱ ክፍል አንድ

(ደቂቀ ናቡቴ መስከረም 24,2005 ዓ.ም ከሐመር መፅሄት የተወሰደ(. ያረጋል አበጋዝ)) ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ኃይለ ቃልን ከትርጓሜ ትርጓሜን ከምሥጢር እንዲሁም ደግሞ ምሥጢርን ከዜማ ጋር አስተባብረውና አስማምተው የሚደርሱ ሊቃውንት ባለቤት ናት፡፡
በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አምሥቱን ጸዋትወ ዜማ ሲደርስ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው አባ ጊዮርጊስ ደግሞ ሰዓታትን ደርሷል፡፡ በዚሁ ዘመን አባ ጊዮርጊስ ጋር ጥልቅ መንፈሳዊ ፍቅር የነበረው አባ ጽጌ ድንግልማኅሌተ ጽጌየተባለውን ድርሰት ደርሷል፡፡ ማኅሌተ ጽጌ ግጥማዊ አካሄድ ያለው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ነው፡፡ ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ የሚውለው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የስደት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊት በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድና መንከራተት እያሰቡ የሚደርስ ምሥጋናና ጸሎት ነው፡፡

በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት (ዘመነ ጽጌ) ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ፡፡ የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔር፣ ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማ ይልቁን እንዴት፡፡ እንግዲህ ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን፣ ምንስ እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ›› (ማቴ 5÷28-33) በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡

እንዲሁም ክቡር ዳዊትተዘከር እግዚኦ ከመመሬት ንሕነ፡፡ ሰብእሰ ከመ ሣዕር መዋዕሊሁ፣ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ - አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ፣ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው፡፡ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፣ ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና›› (መዝ 102÷14-16) በማለት እንደተናገረው የሰው ሕይወት በሣር ይመሰላል፡፡ ሣር አድጐ አብቦ ከዚያ በኋላ ይደርቅና በነፋስ አማካኝነት የረገፈው ሣር እየተነሳ የነበረበት ቦታ ስንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ይሆናል፡፡ ሰውም ከአደገ በኋላ በሕማም ፀሐይነት ይደርቅና በሞት ነፋስነት ይወሰዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ የነበረበት ቦታ ይዘነጋል፡፡ ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ሰው ዘመኑ እንደ አበባ በቶሎ የሚረግፍ መሆኑን በማሰብ ይህ ዘመን ሳያልፍ መልካም ሥራ ለመሥራት ትንሣኤ ኅሊና የሚነሣበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዘመነ ጽጌ የሠራው ድጓም ይህንኑ የሰውን ዘመን አጭርነት፣ የሕይወቱን ኢምንትነት፣ በዚህ ሕላዌ የተፈጠረ ሰው በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መሥራት እንደሌለበት፣ ሁልጊዜ በተዘክሮተ ሞት (ሞትን በማሰብ) እንዲኖር የሚያስረዳ ነው፡፡
በዘመነ ጽጌ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ድጓ በተጨማሪ ከላይ እንደተቀሰው 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣው አባ ጽጌ ድንግል ከዚሁ ዘመን ጋር የተያያዘ ድርሰት ደርሷል፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞች ያሉት ሲሆን ብዛቱም 150 ያክል ነው፡፡ ይህም ድርሰት ‹‹ማኅሌተ ጽጌ›› በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ፍሬ ከአበባ÷ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘው ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ. እርሷን በፍሬ ሲመስል ደግሞ ልጇን በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ፣ ወየዓርግ ጽጌ እም ጕንዱ - ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል›› (ኢሳ 11÷1) ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን እመቤታችንን በበትር፣ ከርሷ የሚገኘውን ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል፣ ከዚያው በማያያዝ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር፣ በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡

እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን ማኅሌተ ጽጌን እንዲደርስ አድርጋዋለች፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ማኅሌተ ጽጌ በመልክዕ አደራረስ ሥርዓት የተደረሰ ሲሆን ይህንንም ለመመልከት እንዲያመች በሚከተሉት ክፍሎች ከፋፍሎ ማቅረብ ይቻላል፡፡ 
ምሥጢር
በዚህ ርዕስ ጉዳይ የምናየው በብሉይና በሐዲስ የተነገረውን እያመሰጠረ፣ በብዙ አምሳልና ትንቢት ይነገር የነበረውን የአምላክን ከድንግል መወለድ፣ ትንቢቱን ከፍጻሜው ጋር እያዛመደ የሚናገረውን ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ የተወሰኑትን እናያለን፡፡
ብኪ ተባረኩ ወተቀደሱ አሕዛብ፣
ትእምርተ ግዝረቱ ወዘርዑ ለአብርሃም አብ፣
ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ውሁብ፣
ማርያም ዕፀ ሳቤቅ ወምሥራቅ ዘያዕቆብ፣
ወላዲቱ ለሥርግው ኮከብ››

ትርጉም
‹‹አሕዛብ በአንቺ የተባረኩብሽ፣ የአብርሃም የግዝረትና የዘሩ ምልክት አንቺ ነሽ፡፡ የድንግልናሽ ጽጌ በግዕ (በግ) የይስሐቅ ቤዛ ሆኖ ተሰጠ፡፡ ማርያም ሆይ የተወደደውን ኮከብ የወለድሽ የያዕቆብ ምሥራቅ ነሽ፡፡››

እግዚአብሔር አብርሃምን ከሀገሩና ከወገኑ ተለይቶ እርሱ ወደሚያሳየው ሀገር እንዲሄድ ካዘዘው በኋላ ‹‹በዘርከ ይትባረኩ ኩሎሙ አሕዛበ ምድር፤ በዘርህ የምድር አሕዛብ ይባረካሉ› (ዘፍ 12÷3) ብሎ ቃል ኪዳን፣ ከአሕዛብ የሚለይበትና እግዝአብሔርን የሚያመልክ መሆኑ የሚታወቅበት ምልክት የሚሆን ግዝረትን ሰጠው፡፡ እንዲህ ሲል፡- ‹‹በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳን ይህ ነው፡፡ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፡፡ በእኔና በአንተ ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል›› (ዘፍ 17÷9-11)፡፡አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉየሚለው ተስፋ በይስሐቅ አልተፈጸመም፡፡ ምክንያቱም በሰው ላይ የተጣለው ርግማን በይስሐቅ አልተወገደም÷ በይስሐቅ የሚወገድ ቢሆን ኖሮ ይስሐቅ በተሰዋና ዓለምን ባዳነን ነበር፤ ክርስቶስም ወደዚህ ዓለም መምጣትና መሞት ባላስፈለገው ነበር፡፡ ስለዚህ በዘርህ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ተብሎ ለአብርሃም የተነገረው ተስፋ የተፈጸመው ክርስቶስ ከእመቤታችን በድንግልና ሲወለድ ወይም ሰው ሲሆን ነው፡፡ አምላክ ሊዋሐደው የሚችል ንጹሕ ሥጋና ነፍስ ይዛ ተገኝታ ለአብርሃም የተነገረውን ተስፋ እንድናገኝ አድርጋለችና፡፡
 ለአብርሃም የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ያን ጊዜ ያመነና ያላመነ የሚለው በግዝረት እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ደግሞ በሕዝብና በአሕዛብ መካከል መለያው ምልክቱ ጥምቀት ነው፡፡ ከአሕዛብ የሚለየንን፣ የእግዚአብሔር ልጆችና የመንግሥቱ ወራሾች የሚያደርገንን ጥምቀት ተጠምቆ ‹‹ተጠመቁ›› ያለንን ክርስቶስን ያገኘነው ከእመቤታችን በመወለዱ ነው፡፡ ለዚህ ነው፡-
ዘብኪ ተባረኩ ወተቀደሱ አሕዛብ፣
ትእምርተ ግዝረቱ ወዘርሁ ለአብርሃም አብያለው፡፡

ክርስቶስ ሰው የሆነው ከአብርሃም ዘር ነው (ዕብ 2÷16)፡፡ ክርስቶስን ያስገኘች እመቤታችን የአብርሃም ዘር መሆኗን ወንጌላዊው ማቴዎስ በምዕራፍ አንድ በሚገባ አስረድቷል፡፡ ለአብርሃም የተሰጠው ተስፋ በእርሷ አማናዊ መሆኑንም ያጠይቃል፡፡

ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ውሁብ
ማርያም ዕፀ ሳቤቅ ወምስራቅ ዘያዕቆብ
ወላዲቱ ለሥርዓው ኮከብ፡፡

ይስሐቅ ለመሥዋዕት በቀረበ ጊዜ ከመሞት ያዳነው በግ ከዚህ መጣ ሳይባል በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ ተገኝቷል (ዘፍ 22÷13)፡፡ አብርሃም በጉን ሰውቶ የታሰረውን ይስሐቅን ፈትቶታል፡፡ ይስሐቅ የዓለሙ ምሳሌ ሲሆን በጉ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ በጉ የተያዘበት ዕፀ ሳቤቅ ደግሞ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ በጉ በዕፀ ሳቤቅ ታስሮ እንደተገኘ ክርስቶስ ሰው የሆነው ከእመቤታችን ነው፡፡ በግ ቤዛ ሆኖ ይስሐቅን ከሞት እንዳዳነው ሁሉ ክርስቶስም ስለ ዓለሙ ኃጢአት ሞቶ ለዓለሙ ቤዛ ሆኖአል (ዮሐ 3÷16-17)፡፡

ደራሲው የተምሳሌቱን መፈጸም ካስረዳ በኋላወምስራቅ ዘያዕቆብ. . .› ይላል፡፡ በለዓም ‹‹ኮከብ ይሰርቅ እምያዕቆብ፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ኃጢአተኝነትንም ከእስራኤል ያስወግዳል…›› ብሎ ትንቢት የተናገረለትን ኮከብ የወለደች እርሷ መሆኗን የሚያስረዳ ነው (ዘኁል 22÷17 ኢሳ 27÷9 59÷20 ሮሜ 11÷26)፡፡
ሰመዩኪ ነቢያት እስርእዩ ኅቡአተ፣ 
ገነተ ጽጌ ዕፁተ ወኆኅተ ምሥራቅ ኅትምተ፣ 
እግዚአብሔር ወሀበ እንዘ ይብል ለቤተዳዊት ትእምርተ 
ከመ ትፀንሲ ድንግል ወትወልዲ ሕይወተ 
ኢሳይያስኒ ነገረ ክሡተ፡፡ 
ትርጉም
‹‹ምሥጢርን ያዩ ነቢያት የተዘጋች የምሥራቅ በር የታተመች ገነት እያሉ ጠሩሽ፡፡ እግዚአብሔር ለዳዊት ቤት ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ በኢሳይያስ አማካኝነት በግልጽ ተናገረ፡፡››

ከሩቅ ያለውንና ወደፊት የሚሆነውን በትንቢት መነጽር አቅርበው ያዩና ሥውሩ ምሥጢር የተገለጠላቸው ነቢያት ‹‹ገነተ ጽጌ ዕፁተ፣ ወኆኅተ ምሥራቅ ኅትምተ፤ የታተመች ፈሳሽ የተዘጋች የምሥራቅ በር›› እያሉ ጠሩሽ፡፡

ሰሎሞን በመኃልዩ፡- ‹እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈች ገነት÷ የተዘጋች ምንጭ፣ የታተመች ፈሳሽ ናት›› ይላታል፡፡ በዚህም እመቤታችንን፡-
/ በተቈለፈች ገነት
/ በታተመች ምንጭ መስሏታል፡፡ ለምን?

/ የተቈለፈች ገነት
በውስጥዋ አትክልት ሲኖር ነገር ግን ወደዚህች ቦታ የሚደርስ የለም፣ ተቈልፏልና፡፡ እመቤታችንም በንጽሕናና በድንግልና የታጠረች ስለሆነች ከእርስዋ የተወለደ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡

የተክል ቦታ ዘር ሳይዘራባት ወይንም ተክል ሳይተከልባት እንዲሁም የሚንከባከበው ሳይኖር ሊያፈራ አይችልም፡፡ ይህች ገነት ምንም ነገር የማይደርስባት የተቆለፈች ስትሆን አትክልት ግን አለባት፡፡ እመቤታችንም በድንግልናና በንጽሕና የፀናች ስትሆን እንበለ ዘር (ያለ ወንድ ዘር) ክርስቶስን አስገኝታለች፡፡
   
/ የታተመች ምንጭ
ምንጩ የታተመ ሲሆን ነገር ግን ውኃ ያለው ነው፡፡ እመቤታችንም በድንግልና የፀናች ስትሆን በእናትነት ክርስቶስን ወልዳለች፡፡ ሕዝቅኤልም ‹‹ወርኢኩ ኆኅተ በምሥራቅ፣ ኅቱም በዐቢይ መንክር ማኅተም አልቦ ዘቦኦ ዘእንበለ እግዚአ ኃያላን ቦአ ውስቴታ ወወጽኣ…››፡፡

‹‹ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራልአለኝ›› ይላል (ሕዝ 4÷1-3)፡፡

የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ማለቱ ከሦስቱ አካል አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ፍፁም ሰው ሆኖ ከእርስዋ ተፀንሶ ተወልዷልና ነው፡፡

ይህ ሕዝቅኤል ያየው ሕንፃ በጥሬ ትርጉሙ ተወስዶ ቤተ መቅደስ ነው እንዳይባል ቤተ መቅደስ የሚሠራው ሕዝቡ አምልኮቱን ሊፈጽምበት ስለሆነ ከተሠራ በኋላ ለምን ይዘጋል? ‹በመካከላቸው አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝእንዲል (ዘጸ 25÷8)፡፡ 
ይኸው ነቢይ ስለ ቤተመቅደስ በተናገረበት ቦታ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹…ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የደኅንነቱን መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት›› ይላል (ሕዝ 46÷12)፡፡ ሰሎሞንና ሕዝቅኤል ስለ እርስዋ የተምሳሌትነትና በትንቢት የተናገሩላት እርስዋ ድንግል ማርያም መሆኗን ከዘከረ በኋላ ነቢያት ብቻ ሳይሆኑ ራሱ እግዚአብሔርም ምልክት መስጠቱን እንዲህ ሲል ይገልጻል፡፡
‹‹እግዚአብሔር ወሀበ እንዘ ይብል ለብተ 
ዳዊት ትእምርተ ከመ ትፀንሲ ድንግል ወትወልዱ ሕይወት 
ኢሳይያስኒ ነገረ ከሡተ›› ይላል፡፡ 
ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፣ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች›› (ኢሳ 7÷13-14) በማለት እግዚአብሔር ሰውን ይቅር የማለቱና የሰጠውን ተስፋ የመፈጸሙ ምልክት የእመቤታችን ክርስቶስን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና መውለድ መሆኑን ተናገረ፡፡

መልአኩ ለእረኞች የጌታችንን መወለድ ብሥራት ከነገራቸው በኋላ ሄደው እንዲያገኙት ሲልካቸው ‹‹ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፣ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ›› ነበር ያላቸው (ሉቃ 2÷12)፡፡ ሰብአ ሰገልም ‹‹ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት›› (ማቴ 2÷11)፡፡ የድኅነታችን ምልክት የክርስቶስ በድንግልና ከእመቤታችን መወለድና መታየት ነው፡፡ እኛም እንደ ሰብአ ሰገል እውነተኛውን ክርስቶስን የምናገኘው ከእናቱ ጋር ነው፡፡ የእውነተኛ ሃይማኖት ምልክትም ናት፡፡ ክርስቶስን በእኛ ባሕርይ ከመውለዷም በላይ በስደቱ፣ በመዋዕለ ትምህርቱ፣ በስቅለቱ፣ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት ሲያድል ሁሉ አልተለየችም፡፡ ስለዚህ እኛም ረቂቅ ምሥጢርን ዐይተው በተለያየ ስያሜ እንዳመሰገኗት ነቢያት ልናመሰግናት ይገባል፡፡ ይኸውም የሚጠቅመው ራሳችንን ነው፡፡ እርስዋማ ምን ጊዜም የተመሰገነች ናት፡፡

ማዕረረ ትንቢተ ማርያም ዘመነ ጽጌ እንግዳ
ወዘመነ ፍሬ ጽጋብ ዘዓመተ ረኃብ ፍዳ
ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ
ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውግሪሁ ለይሁዳ
ፀቃውዓ መዓር ጥዑም ወሀሊብ ፀዓዳ፡፡

ትርጉም
በመከር ጊዜ አበባ፣ በአበባ ጊዜ ደግሞ መከር አዝመራ ማጨድና መሰብሰብ የለም፡፡ ምክንያቱም ጊዜያቸው የተለያየ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ በመስከረም ወር የአበባ ጊዜ በመሆኑ አዝመራ መሰብሰብ የለም፡፡ የትንቢት መከር መካተቻ የሆንሽ እንደ ዘመነ ጽጌ የረሃብን ዘመን ያስወገድሽ ማርያም ሆይ፣ የኤልዳ ነቢይ ኢዩኤል ከይሁዳ ተራሮች ጣፋጭ ማርና ፀዐዳ ወተት ይፈሳል ብሎ የተናገረው ትንቢት በአንቺ ታወቀ፣ ተፈጸመ፡፡ እመቤታችን ነቢያት የተናገሩት የትንቢት ዘር ተፈጸመባት፡፡ ማለትም ነቢያት የአምላክን ሰው የመሆን ነገር በተለያየ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡ ጌታችን ነቢያት የተናገሩት ትንቢት መፈጸሙንና ይህንን ፍጻሜ ለማየት የታደሉት ሐዋርያት መሆናቸውንአንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳልየሚለው ቃል እውነት ሆኗል፡፡ እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኳችሁ፡፡ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ› በማለት ተናግሮአል (ዮሐ.4÷37-38)፡፡ ይህም ነቢያት የዘሩት ትንቢት በሐዋርያት ዘመን ለአጨዳ ለፍሬ መድረሱን መናገሩ ነው፡፡ ስለሆነምማዕረረ ትንቢትየትንቢት መካተቻ ማርያም አላት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍሬ ክርስቶስን ያስገኘችና ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለችእየተባለ የተነገረላት በመሆንዋ በአበባ ትመሰላለች፡፡

ስለዚህ እመቤታችን በመከር ወራት የምትገኝ አበባ ናት፡፡ በመከር ጊዜ የአበባ መገኘት ያልተለመደ ስለሆነወዘመነ ጽጌ እንግዳ - እንግዳ የሆነ አበባአላት፡፡ ከዚህ በኋላብኪ ተአምረ ዘይቤ ነቢየ ኤልዳ፣ ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውጋሪሁ ለይሁዳ፣ ፀቃውዓ መዓር ጥዑም ወሀሊበ ፀዓዳ›› በማለት ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረውን ትንቢት አፈጻጸም ይናገራል፡፡

ነቢዩ ኢዩኤል በዘመኑ ጽኑ ረኅብ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን በምሕረት እንደሚጐበኛቸውና ረሃቡ እንደሚጠፋ ይነግራቸው ነበር፡፡ብዙ መብል ትበላላችሁ÷ ትጠግቡማላችሁ፣ ከዚህ በኋላ እንዲህ ይሆናል፣ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠበጥባሉ÷ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ÷ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ› (ኢዩ 3÷18 2÷26)፡፡

ይህም የእግዚአብሐርን ጸጋ ሁላችንም በመቅረብ እንድናውቅና ማኅሌተ ጽጌ በመጸለይና ማኅሌቱን በመቆም የእመቤታችንን በረከትና ረድኤት የልጇን የክርስቶስን ምሕረት ለማግኘት ያበቃናል፡፡ ለዚህም እመ አምላክ ድንግል ማርያም በረድኤቷና በበረከቷ አትለየን፡፡

No comments:

Post a Comment