Wednesday, October 3, 2012

†♥† ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ†♥† መዝ.111፡1-6



በሰመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
†እንኳን ለአባታችን ለጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የበዓላቸው  መታሰቢያ  በሰላም አደረሰን።†
“ጻድቅ በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል እውነት እላችኋለሁ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም። "  የማቴዎስ ወንጌል ፲፡፵­-፵፪ (1040­-42)
ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ የጸድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል መዝ.111፡1-6 ምሳሌ 10፡7 ማቴ. 10፡40-42
ቅድመ ዓለም ዘሀሎ አለም ከመፈጠሩ በፊት ለነበረ ለእግዚአብሔር አብ እና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ለለበሰ ለእግዚአብሔር ወልድ እንዲሁም ከእነሱ ባለመራቅ ለሚኖር  ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፡፡ የአባቴ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ነገር እና መልክአ በማብዛት አይደለም በማሳነስ በማስረዘም አይደለም በማሳጠር እንድጽፍ ያነሳሳኝ ክብርና ምስጋና ጌትነትና ውዳሴ ይገባዋል አሜን በእውነት፡፡


አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ . ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡ ተክለ ሃይማኖት ማለት ደግሞ ተክለ አብ ተክለ ወልድ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው፡፡


በወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በአሥራ አምስት ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ /ጌርሎስ/ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ኃሃይማኖት» አለው፡፡ ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡


አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ

«አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡»

/ገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕ. ፳፰ -

ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ሃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲገልፅ:-
«
እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» /ዕብ. ምዕ ፲፩ ፴፫ / እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡

«ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡
«
የአንበሶችን አፍ ዘጉ» ምዕ ፲፩ ፴፫ /ምዕ ፲፩ ፴፬ /እንዳለው አባታችንም የአውሬውን የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጠዋል።
«
ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡
«ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡
ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁእያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡

በመጨረሻም አባታችን በነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸው ሆነ። በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ለእኚህ ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለ ሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬ ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡
“የጸድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ሃይልን ታደርጋለችና::” ያዕ. 5፡15-16 
ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ/የጸድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል መዝ.111፡1-6 ምሳሌ 10፡7 ማቴ. 10፡40-42 … ጻድቅ በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል እውነት እላችኋለሁ ዋጋውም አይጠፋበትም…  
ለጽንሰትከ፡- ተክለ ሃይማኖት ሆይ አስቀድሞ በማህጸን ለተጸነስከው ጽንሰትህና በታህሳስ 24 ቀን ለተወለድከው ልደትህም ሰላም እላለሁ፡፡
ለዝክረ ስምከ፡- ተክለ ሃይማኖት የስምህ የመነሻ ፊደሉ ትእምርተ መስቀል ለሆነው ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁኝ እርሱም ገናናና የከበረ ስም ነውና፡፡
ለስእርተ ርዕስከ፡- ተክለ ሃይማኖት ሆይ በአምላክ ህሊና   ለሚቆጠሩና ለሚታሰቡ የራስ ጸጉሮችህ ሰላም እላለሁ እሊኸውም የክብር መጎናጸፊያ ያላቸው እንደ ሦስቱ የይሁዳ ልጆች  ናቸውና፡፡
ለርዕስከ፡-  ተክለ ሃይማኖት ሆይ መልከ መልካማ ሙሽራ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን በንጹህ የአፌ ወርቅ ለመሰለችው ርዕስህ ሰላም እላለሁ፡፡
ለገጽከ፡- ተክለ ሃይማኖት ሆይ ከጸሃይ ከጨረቃ ስነጸዳል ይልቅ ለክርስቶስ የምስጋና ጸዳል ለተዋበው ፊትህ ሰላም እላለሁ
( ከጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መልከዓ ላይ የተወሰደ፡፡)

እግዚአብሔር ለአባታችን ቃል ኪዳን የሰጣቸው “ስምህን የጠራ፣ ዝክርህን የዘከረ፣ በስምህ እንግዳ ለተቀበለ፣ በስም ለተራበ ያበላ፣ ለተጠማ ያጠጣ፣ ሰው ሁሉ እኔ እስከ ትውልድ እምርልሃለሁ" ቤትህን የሰራ በሰማይ የመንግስት ቤት እኔ ቤት እሰራለታለሁ።“የገድልህን መጽሐፍ የጻፈ፣ ያጻፈ፣ ያንተን አማላጅነት በመተማመን ለጸለየው” በሰማይ በሕይወት መጽሐፍ እኔ ስማቸውን እጽፋለሁ በማለት ቃል ኪዳን ገብቶላቸው ሦስት ጊዜ ስማቸውን ከጠራና ሰላምታ ከሰጣቸው በኋላ ወደ ሰማይ አርጓል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ  ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡
ምንጭ፡- መዝገበ ታሪክ፣ ነገረ ቅዱሳን ፪።

2 comments: