በአብ ስም አምኜ አብን
ወላዲ ብዬ፣ በወልድ ስም አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሰራጺ ብዬ በማመን ምንም እንኳን
በስም በአካል በግብር ሦስት ቢሆኑም በመለኮት ዓለምን በመፍጠርና በማሳለፍ በህልውና በመፍረድ አንድ አምላክ ብዬ በማመንና
በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በመታመን ስለ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ከብዙ በጥቂቱ ለመጻፍ እንዲህ እንጀምራለን።
“…. ከመ እግነይ
ለስምከ እግዚኦ ኪያየ ይጸንሑ ጻድቃን እስከ ሶበ ተዐስየኒ።” (“ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ።”) መዝ.፻፵፩፡፯ (141፡7)
†♥†አባ
ሳሙኤል ዘዋልድባ†♥†

ዛሬ በዋልድባ የሚያመሰግኑበት ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያምን ከተከዜ ወዲህ ያመጡ እሳቸው ናቸው። ይህን እየጸለዩ ሲሄዱ ክንድ ከስንዝር መሬት ለቀው ይታቱ ነበር። አንድ ቀንም ይህንን ጸሎት ደግመው ውኃውን ሲባርኩት ኀብስተ ሕይወት ሆነላቸው። ከነ ደቀመዛሙርቶቻቸው ተመግበውታል። እመቤታችን የፍቅር መግለጫ ነጭ ዕጣንና ዕንቁ ሰጥታቸዋለች። ውዳሴዬን ከቅዳሴዬ አንድ አድርጎ የደገመውን አንተ ከገባህበት መካነ ሕይወት (የሕይወት ቦታ) አስገበዋለሁ ብላ ተስፋ ሰጥታቸዋለች። ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ ጌታ በስብሐተ መላዕክት ተገልጾ በስምህ የተማጸነውን በጎ የሰራውን ዜና ገድልህን የጻፈ፣ ያጻፈ፣ የያነበበ፣ የተማረ፣ የያስተማረውን፣ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ ምሬልሃለሁ። በዚህ ቦታ የሚሰበሰቡ ልጆችህን ከእዳ ከፍዳ እሰውርልሃለሁ። አላቸው። እንኪያስ ቦታዋን ባርክልኝ ብለው እንደ መሶብ አንስተው አስባርከዋት በገዳመ ዋሊ ታኀሳስ ፲፪ (12) ቀን ዐርፈዋል። የአባታችን ረድኤትና በረከታቸው በሁላችን ላይ ለዘላለሙ ጸንቶ ይኑር አሜን።
“በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው። ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና።“ ፊሊ.፫፡፩-፫
(ፊሊ.3፡1-3
ምንጭ፡- በማኀበረ
ቅዱሳን ትምህርት ክፍል የተዘጋጀ ነገረ ቅዱሳን ቁጥር ሁለት መጽሐፍና የኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ታሪክ በሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ
አረጋ የተዘጋጀ።
እድሜ ለንሰሐ ዘመን ለፍሰሃ ሰጥቶኝ ይህችን ታህል ስለ አባታችን እንድመሰክር የረደኝ አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።
አመስግኛት የማልሰለች፣ ስለሷ ተናግሬ የማይደክመኝ፣
የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣
የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው
ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ
ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡
kalehiwot yasemalin!
ReplyDelete