Monday, October 22, 2012

ቅዱስ ላልይበላ



በአብ ስም አምኜ አብን ወላዲ ብዬ፣ በወልድ ስም አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሰራጺ ብዬ በማመን ምንም እንኳን በስም በአካል በግብር ሦስት ቢሆኑም በመለኮት ዓለምን በመፍጠርና በማሳለፍ በህልውና በመፍረድ አንድ አምላክ ብዬ በማመንና በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በመታመን ስለ ስለ ቅዱስ ላልይበላ ከብዙ በጥቂቱ ለመጻፍ እንዲህ እንጀምራለን።

“…. ከመ እግነይ ለስምከ እግዚኦ ኪያየ ይጸንሑ  ጻድቃን እስከ ሶበ ተዐስየኒ።” (“ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ።”) መዝ.፻፵፩፡፯ (141፡7)

ቅዱስ ላልይበላ /ከ1180­-1207 ዓ.ም/
ቅዱስ ላሊበላ አባቱ ጃን ስዩም እናቱ ኪርወርና ይባላሉ። መጋተ ፳፱ ቀን ተፀንሶ ታህሳስ ፳፱ ቀን ተወለደ። በተወለደም ጊዜ በንብ ስለ ተከበበ እናቱ ማር የበላል ለማለት "ላል ይበላል" ብላለች። በአገውኛ ላል ማር ማለት ነው። ከዚህ የተነሳ ስሙ ላሊበላ ተባለ። ቅዱስ ላሊበላ የብሉያትንና የሐዲሳትን ትምህርት ትርጓሜ የተማረና ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው። ትርጓሜ መጽሐፍትንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያነን ተምሮ ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ሮሃ ሲመለስ ንጉሱ የአባቱ ልጅ ታላቅ ወንድሙ ሐርቤ (ገ/ማርያም) ተቀብሎ ሥርዓተ መንግስትን እያስተማረ ከእርሱ ጋር አስቀመጠው።
ይሁን እንጂ መኳንንቱና ሹማምንቱ  ስለ ቅዱስ ላሊበላ የተናገረውን ትንቢት የሚፈጸም መሆኑን ለንጉሱ እየነገሩ በጥላቻ እንዲመለከተው አደረጉ። ንጉሱ ከሀገር ለማባረር አለበለዚያ ለመግደል በሚያወጣ  በሚያወርድበት ጊዜ ለንጉሱ የእናትም የአባትም ልጅ የሆነች ለቅዱስ ላሊበላ ግን የአባቱ ልጅ ብቻ የሆነች ዮዲት ቅዱስ ላሊበላ ለመግደል ተንኮል መጠንሰስ ጀመረች። ቅዱስ ላሊበላ ግን ጌታችን  በዕለተ ዓርብ የጠጣውን ሐሞትና ኮምጣጤ ለማሰብ ሁል ጊዜ አርብ አርብ ኮሶ ይጠጣ ነበርና እንደተለመደው ኮሶውን አዘጋጅተሽ ላኪልኝ ሲላት ለተንኮሏ ስለተመቻት ደስ አላት። ስለዚህ መርዛ ቀላቅላ ላከችለት። ተልኮ ያመጣውም ቀምሼ እሰጣለሁ ብሎ አንዴ ቢጎነጭለት ወዲያውኑ ሙቶአል። ላሊበላም ይህ ሁሉ የሆነው በኔ ምክንያት አይደለምን ብሎ የተረፈችዋን ጨለጠው። ቅዱስ ገብርኤልም ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ ከሥጋቅ ሙቀት ልምላሜ ሳይለይ ከጌታ መንበር ፊት አደረሰው። ሰባቱ ሰማያት አስጎበኘው። ጌታችንም ኢየሩሳሌም ለመሄድ ተነስተው በበረሃ የሚቀሩ ወገኖች አስቤያለሁና በተወለድክባት በሮሃ ኢየሩሳሌምን ትሰራታለ፤ አንተ የምትሰራውን ማንም አይሰራም አለው። ከትህትና የተነሳ ብዙ ቢከራከርም ጌታችን አስረድቶትቃል ኪዳን ተቀብሎ ተመልሷል። ታሪኩ ረጅም ቢሆንም እያሳጠርኩ ስመጣ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ላሊበላን በክንፎቹ ነጥቆ ወስዶ ኢየሩሳሌም አስጎብኝቶታል። በዚያ ቅዱሳት መካናትን አይቶ እጅ ነስቶ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ በደስታ ተመስጦ ሳለ ጌታ በብሩህ ደመና ተገልጾ በተስፋ የጸናውን በኪዳን የተማጸነውን ከርደተ ገሃነም አድንልሃለሁ። መቃብርህን የተሳለመ መቃብሬ ጎሎጎታን እንደተሳለመ ይሆንለታል ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶለታል።ከዚህ በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ዳግመኛ በክንፉ ነጥቆ መስቀለ ክብራ ካለችበት ገዳም አድርሶት ተሠወረ። በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር በሕልም ለንጉሡ መንግትህን ለወንድምህ ለላሊበላ ሰጥተህ ህልፈት የሌለበትን መንግስተ ሰማያትን ፈልግ ብሎት መንግስቱን ለላሊበላ  አስረክቦ ከበረሃ ወድቆ ከፍጹምነት ደርሶ አርፏል።
ቅዱስ ላሊበላም መንግስቱን ከያዘ በኋላ በየሀገሩ ብዙ አብያተ ክርስታያናትን ያሰራ ሲሆን በከተማው በደብረ ሮሃ ­፲፩ አብያተ ክርስቲያናትን ከቋጥኝ አስፈልፍሎ አሠርቷል። እኚህም

፩. ቤተ አማኑኤል                ፯. ቤተ ጎልጎታ
፪. ቤተ መድሃኔዓለም             ፰. ቤተ ጊዮርጊስ
፫. ቤተ ማርያም                 ፱. ቤተ መርቆሬዎስ
፬. ቤተ ሚካኤል                 ፲. ቤተ ሊባኖስ
፭. ቤተ ገብርኤል               ፲፩. ቤተ ደናግል ናቸው።
፮. ቤተ መስቀል         
እንዲህ አብያተ ክስቲያናትን ሲሰራ አጥቶ እስከ መቸገር ደርሶ ገንዘቡን ለድሃ ሲመጸውት ለጸሎ ሲተጋ ኖሮ ሰኔ ፲፪ በክብር አርፏል። የቅዱስ ላሊበላ በረከቱን ረድኤቱ ቃልኪዳኑ አይለየን አሜን።
የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር  በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡
በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡
ሌሊትና ቀን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑና ሳይሰለቹ የሚጠብቁን ሊቀነ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ሩፋኤል ቅዱስ ዑራኤል ቅዱስ ራጉኤል ቅዱስ ፋኑኤል እልፍ አእላፋት የሆኑ ጠባቂ መላእክት ሳመሰግን በደስታ ነው፡፡
በጸሎታቸው ያልተለዩኝን ጻድቃን አባቶቼን አቡነ ተክለሃይማኖትን አቡነ ገብረምንፈስ ቅዱስን አቡነ ሀብተማርያምን አቡነ አረጋዊን አቡነ ኪሮስንና ሌሎች ቅዱሳን አባቶቼን እንዲሁም እናቶቼን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራን ቅድስት አርሴማን ብዙ ያልጠቀስኳቸው ቅዱሳንን ለማመስገን ቃላት የለኝም፡፡
በሰማዕትነታቸው የጥንካሬ ምሳሌ የሆኑልኝ በጸሎታቸው የረዱኝን  ቅዱሳን ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ቅዱስ እስጢፋኖን መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስንና ሌሎችን ቅዱሳን ሰማዕታትን ሁሉ በእጅጉ አመሰግናለሁ ለዘላለሙ አሜን፡፡ 
ምንጭ፤- ነገረ ቅዱሳን ቁጥር ፪፣ መዝገበ ታሪክ፣ ስንክሳር  

የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ  ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment