በስመ አብ
ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡
አሜን፡፡
†♥† አባ
ዮሐንስ
ሐጺር†♥† ( ጥቅምት ፳ አዕረፈ)
†♥† “ከቡር ሞቱ
ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር (የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።”) መዝ.፻፲፭/፻፲፮፡፲፭
(115/116፡15
†♥†
“እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡“ (እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“”†♥†
መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)
†♥† በዚህች ቀን አባ ዮሐንስ ሐጺር አረፈ። ቁመቱ አጭር ስለሆነ ነው ዮሐንስ ሐጺር የተባለው። በ18 ዓመቱ በገዳመ አስቄጥስ መንኩሶ በተጋድሎ የኖረ ሲሆን ይህ አባት “ነጽሮተ ስሉስ ቅዱስ” የደረሰ አባት ነው።
†♥†እዚህ ደረጃ የደረሱ አባቶች ቀና ቢሉ ሥላሴን ይመለከታሉ ዝቅ ቢሉ እንጦሮጦስን ያያሉ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የገዳሙ አበምኔት ሊፈትነው ብሎ ደረቅ እንጨት ሰጠው ይህንን ተክለህ አለምልመህ ፍሬውን አምጣልኝ አለው።
†♥†እርሱም እንጨቱን ተከለውና፤ 3 ዓመት ሙሉ ከሩቅ ቦታ ውሃ እየቀዳ አጠጣው። በ3ኛው ዓመት ጸደቀ፤ ለመለመ፤ ትልቅ ዛፍም ሆነ፤ ፍሬም አፈራ፤ መነኮሳቱ ይህ የትእግስት ውጤት ነው ብለው ፍሬውን ቀምሰውለታል፡፡
†♥†አንዲት “አትናስያ” የምትባል ሴት ነበረች። መጀመሪያ ጻድቅ ነበረች በኋላ ላይ በዝሙት ወደቀች ዘማዊም ሆነች። የቀድሞ ቅድስናዋን የሚያውቁ መነኮሳት ሊመክሯት ቢመጡ ሳቀችባቸው። አሁን ማንን እንላክ ብለው አሰቡ ዮሐንስ ሐጺርን ላኩት። ተራ ሰው መስሎ ገባ፤ ለዝሙት የመጣ መስሏት ተቀበለችው። ተጫወት አለችው ዮሐንስ ሐጺር ማልቀስ ጀመረ ምን ያስለቅስሃል ትለዋለች።