Wednesday, December 5, 2012

ክብረ ቅዱሳን



በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
የቀበና ምስራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ቤ/ክ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህር እና የሰብከተ ወንጌል ኃላፊ
ክፍል አንድ 

ክፍል ሁለት 
 

የቅድስት ቤተክርስቲያን አባቶች የእርቀ ሰላም ጉባኤ በዳላስ ቴክሳስ ተጀመረ

ምንጭ ፡-
“ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን - ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ”።


አባቶች በጋራ ከጉባኤው በፊት በተገናኙበት ወቅት
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ካህናት አባቶች፣ ዲያቆናት፣ ምዕመናን እና ምዕመናት በጉጉት ሲጠብቁት የነበሩት የቅድስት ቤተክርስቲያን አባቶች የእርቀ ሰላም ጉባኤ ትላንት ረፋዱ ላይ በዳላስ ቴክሳስ በሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በጸሎት ተጀምሮ በመቀጠል በአካባቢው በሚገኘው ሆቴል የድርድሩ እና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ሰላምን ለማምጣት በአባቶቻችን እና በምዕመናን ጸሎት እና ልመና የተሳካ እንደሚሆን የሁሉም ወገኖች እምነት ነው።

Tuesday, December 4, 2012

ታላቅ መንፈሣዊ ጉባኤ December 15 & 16, 2012

ትላንት ዋልድባ ታረሰ፣ ዛሬ የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ሊፈርስ ነው፣ ነገስ . . . በተመሳሳይ ርዕሶችና በእርቀ ሰላሙ ዙሪያ ውይይቶች ተዘጋጅተዋል እንዳያመልጦት!

ዓለምዓቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች አንድነት፣ ቀድሞ ዋልድባን ለመታደግ የተቋቋመው ኮሜቴ ለአራተኛ ጊዜ በወቅታዊ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመጠቆም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ባለሙያዎችን ጋብዞ ለመነጋገር የሁለት ቀናት ተከታታይ ጉባኤ አዘጋጅቷል። የእርሶ ተሳትፎ እየት ድረስ ነው? ለቤተክርስቲያንዎ ሊያበረክቱ የሚችሉትን ለመጠቆም ተዘጋጅተናል፣ ኑ! እንምከር ቤተክርስቲያንን ለተተኪው ትውልድ ከነሙሉ ክብሯ ለማስተላለፍ አብረን እንስራ!
እግዚአብሔር አምላክ ቤተክርስቲያናችንን በረደኤት ይጠብቅልን አሜን

ቅዳሜ Dec. 15, 2012 እሑድ DEC. 16, 2012
St. Andrew UMC ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅ/ማርያም ቤ/ክርስቲያን
845 N. Haward Street 1360 Buchanan Street, NW.
Alexandria, VA 22304 Washington, DC 20018
2:00 – 6:30 pm. 4:00 – 8:00 pm

Monday, November 26, 2012

†አባ ገሪማ ዘመደራ†

አባ ገሪማ ዘመደራ  (“ኦ ወልድዬ ግሩም ገሪማ ገረምከኒ”)

የተሰዓቱ ቅዱሳን ሐዋርያዊ ተልእኮ መቅድም
ተሰዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አልአሜዳ በነገሰ በአምስት ዓመት ነው። እንደመጡት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው በአክሱም ዐስራ ሁለት ዓመት ኖረዋል።     
ተሰዓቱ ቅዱሳን በስም አባ አሌፍ፣ አባ አረጋዊ፣ አባ ጰንጠሌዎን፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጵሕማ፣ አባ አፍአባ ሊቃኖስ፣ አባ ይምዓታ፣ አባ ጉባ ይባላሉ። እኚ አባቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ዝም ብሎ አልተቀመጡም፤ ለሥራቸው በር ከፋች የሆነውን ቋንቋ፣ የሕዝቡን ባህል ጠንቅቀው ካወቁ በኋላ ላይ በአንድ አከባቢ ከመኖር ይልቅ መንፈስ ቅዱስ በመደባቸው ቀጥታ ማስተማርን መርጠው መንፈሳዊ ዓላማቸውን ለማሳካት የአክሱምን ነገስታት እርዳታና ድጋፍ አልተለያቸውም ነበር። እኚው ተሰዓቱ ቅዱሳን የመጡበት ሀገራት ሮም፣ እስያ፣ አንጾኪያ፣ ቁስጥንጥንያ፣ ቂሳርያ፣ ኪልቂያ ሲሆን በነበሩበት ጊዜያትም፡­-
፩. ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አጽንቶልናል።
፪. መጽሐፍትን ተርጉሞልናል።
፫. ስብከተ ወንጌልን አስፋፍተዋል።
፬. ብዙ ገዳማትን መስርተዋል።
፭. ሥርዓተ ምንኩስናን አደራጅተዋል።

Sunday, November 18, 2012

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ክፍል ሁለት

                                                                                                                        በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
‹‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ›› ያለው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አስተምሯል፡፡ /መዝ77.2/ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የመላእክትን አማላጅነት የሚያሳይ ነው፡፡ ሙሉ የወንጌሉ ቃል ከዚህ ቀጥሎ የምናነበው ሲሆን ነጥቦቹን አንድ በአንድ እንመለከታለን፡፡

“ይህንም ምሳሌ አለ። ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም። እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት።ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው።” /ሉቃ13.6-9/ይህን ቃል ጽፎ ያቆየልን ሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስ ቢሆንም ትምህርቱን ያስተማረው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ይህንም ምሳሌ አለ›› ብሎ ታሪኩን በመጀመሩ ትምህርቱ ምሳሌያዊ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም፡፡

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ክፍል አንድ


                                                                                                        በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
ዱሳን መላእክት አማላጆቻችን ናቸው፡፡ ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ተጽፏል፡፡ ይህንንም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጥቀስና ትክክለኛ ትርጉማቸውን በምንረዳበት ጊዜ የምናገኘው ነው፡፡
ሐሳቡን በትክክል ለመያዝና ለማጥናት እንዲረዳን የመላእክትን አማላጅነት በስድስት ዋና ዋና መንገዶች ከፍለን ለማየት እንችላለን፡፡ 
1ኛ. መቆም:- መቆም የሚለውን ቃል ትክክለኛ ትርጉም በመረዳት፡- መቆም የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ እንደየአገባቡም ትርጉሙ የተለያየ ነው፡፡ መቆም የሚለው ቃል ከያዛቸው ትርጓሜዎች አንዱ ማማለድ የሚል ነው፡፡ መቆም ከተኙበት ወይም ከተቀመጡበት መነሣት፣ በእግር ቀጥ ማለት፣ መጽናት፣ በክብር መቀመጥ ወዘተ የሚሉ ሌሎች ትርጓሜያትም አሉት፡፡ ስለዚህ እንደየአገባቡ ታይቶ ይፈታል እንጂ ሁል ጊዜ ቃሉን በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ መመልከት ከስሕተት ላይ ይጥላል፡፡
ለዚህ ሁሉ አገባብ ማስረጃ ብትሻ እነዚህንና ሌሎችንም ጥቅሶች በሚገባ ፈትሽ፡፡ ‹‹የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ›.፣ ‹‹የደመናው ዓምድ ቆመ››፣ ‹‹በሃይማኖት ቁሙ›› (ሉቃ8.44፤ ዘዳ31.15፤ ዘኁ10.12፤ 1ቆሮ16.13) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ መቆም የሚለው ቃል የተለያየ ሐሳብ ይዞ መገኘቱን ልብ ማለት ያሻል፡፡

Tuesday, November 13, 2012

✙የእመቤታችን የስደት ምሳሌ✙



በስመ ሥላሴ
ፈጣን ደመና  
 ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈ እግዚአብሔር እየተቃኘ ቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ዐማኑኤልን ይዛ ወደ ግብጽ የመሰደዷን ነገር ተገልጦለት፤   
“እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።” ኢሳ. ፲፱፡፩ በማለት ከገነት የተሰደድነውን እኛን ወደ ቀደ  ርስታችን እንደመጣ ለማጠየቅና፣ ጠላታችን ዲያብሎስን ከሰዎች ልብ አውጥቶ ለመስደድ፤ ክብር ይግባውና ወልደ እግዚአብሔር ልመናዋ ፈጥኖ በሚሰማላት “ደመና መፍጠኒት” በተባለች በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ ወደ ግብጽ የመሰደዱን ነገር አስቀድሞ ገልጾታል።
ይኸውም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ ንጉሡ ሄሮድስ ክርስቶስን ለመግደል በፈለገ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊው ለዮሴፍ በሕልሙ ተገልጾለት “ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወጉየይ ውስተ ብሔረ ግብጽ” (ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ”) ባለው ጊዜ ይኽ ኢሳያስ የተናገረው ትንቢት ሊፈጸም ምልጃወዋ ፈጥነኖ በሚደርስላት   “ደመና መፍጠኒት” በተባለች በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ ወደ ግብጽ በሄደ ጊዜ የግብጽ ጣዖታት ሁሉ እይተሰባበሩ ሲወድቁ፤ በእነርሱ አድሮ ያስቱ የነበሩት አጋንንት ሁሉ ሸሽተዋል። በመሆኑም እመቤታችን “ደመና መፍጠኒት” ወይም ደመና ኢሳያስ ተብላ ተጠርታለች።

Monday, November 12, 2012

መላእክትን ‹‹ያድናሉ›› ማለት ስሕተት ነውን?

ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
 ለመሆኑ መላእክት ማዳን ይችላሉ ማለት ስሕተት ነውን? ዛሬ ዛሬ ብዙዎች መናፍቃን መላእክትን ‹‹ያድናሉ›› ማለት እንደ ስሕተትና እንደ ክህደት ቆጥረውት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለምን ሲባሉም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› በማለት ያለ አገባቡ ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡፡

በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መላእክት አያድኑም ማለት አይደለም፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ዕድሜ ይስጠን እንጂ ራሱን በቻለ ርእስ በሌላ ጊዜ በሰፊው እንመለስበታለን፡፡ ለዛሬ የመላእክትን ማዳን ከመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ እየጠቀስን እንመልከት፡፡

ቅዱስ ዳዊት በግልጥ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል›› ይላል፡፡ (መዝ33.7) ጥቅሱ ‹‹ያድናቸውማል›› ማለቱን ልብ በሉ፡፡ መላእክት የማያድኑ ቢሆኑ ኖሮ ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ ግልጥ አድርጎ ‹‹ያድናቸውማል›› ይል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ከመሰከረው እውነት የሚበልጥ ዕውቀት አለንን? እርሱ ‹‹ያድናሉ›› እያለ እኛ ‹‹አያድኑም›› ብንል ምን ማለታችን ነው? ይህ ጥቅስ ውሸት ነውን? ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንታዘዘዋለን? እናምነዋለን? ወይስ ልናርመው እንወዳለን?

በሌላም የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ንባብ ውስጥ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ›› በማለት ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን እንደባረከ እናነባለን፡፡ (ዘፍ48.16) በዚህ ጥቅስ ውስጥ መልአክ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ›› እንደሚያድን በግልጽ ተጽፏል፡፡ መላእክት ‹‹ያድናሉ›› ላለማለት እነዚህን ግልጽ ቃላት መላእክት ይጠብቃሉ፤ ይራዳሉ፤ ያግዛሉ በማለት ማድበስበስ ይኖርብን ይሆን? ይህ ሁሉ ዝርዝሩ ሥራቸው ቢሆንም እንደሚድኑም ተጽፏልና ማመን ያስፈልጋል፡፡