- ምእመናን “ቅዱስ አባታችን” ብለው በሙሉ ልብና በፍቅር የሚታዘዙት አባት ይፈልጋሉ፤
- ቤተ ክርስቲያን “እንቁላልና ቲማቲም የሚወረወርበት ሌላ ፓትርያርክ” አያስፈልጋትም፤
(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 9/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 18/2012)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ
ክርስቲያን መንበረ ፕትርክና በ5ኛው ፓትርያርክ አረፍተ ሞት ባዶ ከሆነ ወዲህ ላለፉት 20 ዓመታት ሲያከራክር
የነበረው ርዕሰ ጉዳይ እንደገና፣ እንደ አዲስ መወያያ መሆን ጀምሯል። በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃም፣ በግል ደረጃም
የተለያዩ ሐሳቦችም በመንጸባረቅ ላይ ይገኛሉ። በምእመኑ ደረጃ “ነገረ ፓትርያርክ”ን ከማንሣት በፊት ዕርቀ ሰላሙ
መቅደም አለበት የሚለውን አበክሮ በማቅረብ ላይ ይገኛል። የተለያዩ ደብዳቤዎችንም ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ
አቅርበዋል። በሁሉም በኩል ሥጋት የሆነው ግን ክንደ-ፈርጣማው፣ እጀ ረዥሙ የኢሕአዴግ መንግሥት ለእምነቱ ተከታዮች
ፍላጎት ሳይገዛ “የራሱን ፓትርያርክ” እንዳያስቀምጥ ነው።
