Wednesday, November 23, 2011

የተቃውሞ ሰልፍ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም. የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተቃውሞ ሰልፍ እይታዎች ሙሉዉን ቪሲዲ


ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም. የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በአዲስ አበባ መንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተሐድሶ መናፍቃን ላይ ያደረጉትን የተቃውሞ ሰልፍ የሚያሳይ የ 20 ደቂቃ ቪሲዲ ለዛሬ አቅርበንላችኋል
በሰልፉ ላይ በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ከሚገኙ የ131 ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ያላቸውን የደንብ ልብስ(ዩኒፎርም)እና ነጠላ በመልበስ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምቱ ጉባዔው በተሐድሶ መናፍቃን ላይ እርምጃ እንዲወስድ ሲያሳስቡ ይታያል፡፡ ወጣት የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎቹ ተቃውሞአቸውን በአደባባይ ከማሰማታቸው በፊት ቀደም ባሉት ጊዜያት መዋቅራቸውን ጠብቀው ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትና ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት የተሐድሶ መናፍቃንን ማንነት የሚያጋልጥ ባለ 261 ገጽ የጽሑፍ ሰነድና 14 የምስል እና የድምጽ(VCD) ሰነድ በማስረጃነት ማቅረባቸው ቢታወቅም አደባባይ ለመውጣት እነዳላሰቡ ሆኖም ግን እነ በጋሻው፣ትዝታው፣አሰግድ፣ናትናኤል፣ያሬድና ሌሎችም የተሐድሶ ሎሌዎች ስማችን ጠፋ፣ መድረክ ተከለከልን፣ ተሐድሶ የሚባል የለም ፣ወዘተ….በማለት በለመዱት የግራ ዐይን የአዞ እንባቸው ሕዝቡን ለማሳሳት ሰልፍ እንወጣለን ብለው በማወጃቸው ምክንያት ወጥተው ተቃውሞአቸውን እንዳሰሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቪሲዲው፦
• “የዘማሪ” ትዝታው ሳሙኤልን መደብደብና መዋከብ ኋላም በድንጋጤ ጥግ ላይ ተደብቆ ጥርሱን እየነከሰ መንቀጥቀጥን፣
• የተሐድሶ መናፍቅ አሰግድ ሳህሉን ተንኮሳና መንቀዥቀዥ ኋላም መደንገጥና መሸማቀቅን፣
• የ“ዘማሪት” ቅድስት ምትኩንና “ዘማሪት” የትምወርቅን ድፍረትን፣
• የመናፍቁ ናትናኤል ታምራት በፍርሃት ታጥሮና ጥግ ይዞ መታየትን፣
• የ“መምህር” ተረፈን የመሃይም ድፍረትና በኋላም ቅሌትና ውርደት፣
• የሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴንና የቅ/ማርያም ገዳም አስተዳዳሪ አላዋቂነትና አድርባይነትን፣
• የአዲስ አበባን ሰንበት ት/ቤቶች በወኔ የታጀበ ጠንካራና የተደራጀ ተቃውሞን፣
• የቅዱስ ፓትርያርኩን ብስጭትና ወገንተኛነት፣
• የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊሶችን የተረጋጋ፣ሕጋዊና ሰላማዊ የጸጥታ ማስተባበር ሥራን፣
• የአዲስ አበባ ምዕመናንን እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ቅናት ወዘተ…..በአንጻሩ ደግሞ የተሐድሶ መናፍቃንን ድፍረትና አይን አውጣነት ያሳያል፡፡
• የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ቤተ ክርስቲያናችን በተሐድሶ መናፍቃን አትወረርም የሚል አገር አቀፍ ብሎም ዓለም አቀፍ የሆነ አጀንዳ ይዘው ታይተዋል፤
ቪሲዲው ከ“ዘማሪያኑ” እነ ትዝታው ሳሙኤል፣የትምወርቅ፣ቅድስት ምትኩ፣ምርትነሽ ጥላሁን፣ሃብታሙ ሽብሩ፣ሐዋዝ ተገኝ፣…..ከ“መምህራን” ናትናኤል ታምራት፣አሰግድ ሣህሉ፣ተረፈ፣ጋሻዬ መላኩ፣ስንታየሁ፣በፈቃዱ፣ታሪኩ አበራ….ነበሩበት፡፡የአዲስ አበባ ምዕመናን “ፍንዳታ”እያሉ የሚጠሯቸው የመነኩሴ ቆብ ያጠለቁ የተሐድሶ መነኮሳትም ነበሩበት፡፡
እነበጋሻውና ያሬድ አደመ ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው ማስተባበርን መርጠዋል፡፡ማንነታቸው እንዳይታወቅ ፊታቸውን በሰፊ መነጽር ለመሸፈን የሞካክሩ ኮረዳዎችም በሰልፉ ነበሩበት
ቪሲዲው ኤዲት ስለሚጎድለውና ስለ ድምፁ ጥራትም ይቅርታ እንጠይቃለን። 
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ አሜን።

Monday, November 21, 2011

እኔን ቀበሌ አላከኝም፣ የላከኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው አቡነ ፋኑኤል


  • "እኔን ቀበሌ አላከኝም፣ የላከኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው"
  • "14 ዓመት ደክሜ ከሰራሁት ቤቴ የትም አልወጣም"
  • "ወደዳችሁም ጠላችሁም ከዚህ የትም አልሄድም"
  • "አዎ አዲስ አበባ ላይ ቪላዎች ቤቶች አሉኝ፣ ያንን ትቼ ይህንን ህዝብ ላገለግል መጣሁ"
  • "ከዋሺንግተን ዲሲ እስከ ካሊፎርኒያ የኔ ግዛት ነው"
  • "ከዚህ በኃላ ስደተኛ፣ ገለልተኛ፣ መፃተኛ የሚባል ቤተ ክርስቲያን የለም"

የደብረ ምሕረት የትላንትናው ትዕይንት ይሄን ይመስል ነበር

በትላንትናው እለት በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ላይ የተገኙት አቡነ ፋኑኤል በአዋሳ ላይ ልክ እንዳደረጉት ምንም የምታመጣው ነገር የለም የኔን የላከኝ ቀበሌ አይደለም ቅዱስ ሲኖዶስ ነው በማለት ለበዓል የታደመውን ምዕመን አስገርመውት ውለዋል። ትላንት በጠዋት የተጀመረው የቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ በፓሊስ ውጪው በተቃዋሚ ታውኮ ውሏል። ከሥርዓተ ቅዳሴው በኃላ በመምህር ዘላለም ወንድሙ አማካኝነት የማስፈራሪያ መልዕክት እንዲያስተላልፍ በተሰጠቅ ጥብቅ መመሪያ መሰረት መጥቶ በማያውቅበት የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አውደ ምህረት ላይ ቆሞ ባለሙዋልነቱን


 በሚገባ አረጋግጧል፣ እንደሚታወሰው መምህር ዘላለም ወንድሙ ከዚህ በፊት በቅዱስ ፓትሪያሪኩ ፈቃድ በአቡነ ፋኑኤል አደራጅነት እና አዋቃሪነት በተከፈተው  "የቤተ ክርስቲያን የውጪ ግንኙነት ጽ/ቤት" በሚባለው የሰሜን አሜሪካ የሰባኪያን እና ዘማሪያን ባለሙሉ ሥልጣን የበላይ ኃላፊ በሚል እንደተሾመ ይታወሳል። ለማንበብ እዚህ ይጫኑ በትላንትናው ድራማ ላይ አቡነ ፋኑኤል ለእኔ የሚናገርልኝ ሰው ከሌለ እኔው እራሴ ስለ እራሴ ማንነት እነግራችኃለው ብለው ህዝቡን ስለራሳቸው ግድል እና ድርሳን ሲናገሩ ከግማሽ ሰዓት በላይ አሳልፈዋል መዚህም መሠረት እኔ ልሰራ እንጂ ልከፋፍል አልመጣሁም ስለዚህ ከዚህ በኃላ ስደተኛ ወይም ገለልተኛ ሳንል በተጠራንበት በመሄድ እናገለግላለን በማለት አስጨብጭበዋል፣ እንደእውነቱ ከሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ከለየው ጋር ሄዶ መባረክም ሆነ እናቀራርባለን ብሎ ማለት ሥርዓት አልበኝነታቸውን የበለጠ ያጎላዋል እንጂ የሥራ ሰው መሆናቸውን አያስመሰክርም፡ ከዚህ በተጨማሪ "እኔ የሁሉም አባት ነኝ ማለታቸውም" ነገ የአባ ሰላማ ብሎግ ባለቤቶች (ፕሮቴስታንቶቹም) ቢጠሯቸው የሁሉም አባት ስለሆኑ ሄደው ሊባርኩ ነው ማለት ነው አንባቢ ያስተውል።


አቡነ ፋኑኤልና ካሕን መስሎ የቆመው body gourd
 የዛሬ 5 ዓመት ቅዱስ ሲኖዶስ መድቦኝ እዚህ መጥቼ ነበር፣ ነገር ግን  ሕዝቤብ በሀገሩ ማገልገል አለብኝ ከሚለው ጽኑ ፍላጎቴ የተነሳ ለቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤ ጽፌ አዛውሩኝ በማለት ተዛውሬያለሁ ያሉት አቡነ ፋኑኤል አሁን ደግሞ ለ17 ዓመት ደግሜ በገዛ ገንዘቤ ያቋቋምኩትን ቤቴን እና  ሕዝብ ለገልግል ብዬ አዲስ አበባ ላይ ካሉት ቪላዎቼ እናንተን መርጬ ላገለግላችሁ መጥቻለው ብለዋል። ትላንት ከታዩት አስገራሚው ትዕይንት የህዝቡን ቀልብ የሳበው አባ ፋኑኤል ልክ እንደ ቅዱስ ፓትሪያሪኩ የግል ጠባቂ (body gourd) የካህን ልብስ አልብሰው ጥቁር መነጽሩን ደንቅሮ በተጠንቀቅ ሲጠብቅ እና የሙያውን ሥራ በሚገባ ሲወጣ ቆይቷል፣ የፓሊሱ ግርግር፣ ያቦዲ ጋርዱ ጥበቃ፣ የተቃዋሚዎች ስድብ በቤተ ክርስቲያናችን እስከ መቼ እንደሚቀጥል እና ታቦታችን ፊት እንዲህ አይነት ስድብ እና ውርደት መቀጠል እንደሌለበት የሁላችንም እመነት ቢሆንም አቡኑ ግን ወደዳችሁም ጠላችሁም ከሰራሁት ቤቴ ማንም አያስወጣኝም በማለት "ደርግ እንኳን ሁለት ያለውን አንዱን ነው የነጠቀው፣ እኔ ግን አንድ ስለሆነ ያለኝ እሱንም ስጥ የሚል ህግ የለም" ነበር ያሉት።


በእለቱ ከታዩት በርካታ ካሜራዎች እና ተቃዋሚዎች ጥቂቱ
 ሌላው አስገራሚው ትዕይንት ደግሞ አቡነ ፋኑኤል እስከ ዛሬ ድረስ እርሳቸውንም ጨምሮ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሊቃነ ጳጳሳት በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ተቀማጭ ሆነው ብዙ ሥራዎችንም የሰሩም ነበሩ የሞከሩም ደግሞ ነበሩ ነገር ግን አቡነ ፋኑኤል እርሳቸው የመጀመሪያው ለሥራ የመጡ የቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ እንደሆነ ሲናገሩ ምዕመናኑን ሁሉ አስገርመዋል፣ በተለያየ ጊዜ እየመጡ ያደራጇቸው የገለልተኛ አስተዳደር በሙሉ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ነበር የተናገሩት በመቀጠልም ሁሉንም ይዘው ሥራ ለመስራት እንደተዘጋጁ እና ምዕመናኑንም ገንዘብ ያለህ በገንዘብህ ሙያ ያለህ በሙያህ ተባበረኝ ብለው ነበር የተናገሩት። እንደሚታወቀው የራሳቸውን ዝናና ክብር ሲወራ የሚወዱት አቡነ ፋኑኤል ትላንት የርሳቸውን ገድለ ፋኑኤል የሚያወራ ስለጠፋ "ስለ እኔ የሚናገር ከሌለ እኔው ስለራሴ ልናገር" ብለው ነበር እስቲ ስለ እኔ ገድል ተናገሩ ያሏቸው በሙሉ ለመናገር ባይደፍሩም ሕዝበ ክርስቲያኑን ከንቀታቸው የተነሳ ይሄንን ቤተ ክርስቲያን "ተቃዋሚዎች ጥይት ግዛ ብለው ሲሰጡኝ፣ እኔ ቤተ ክርስቲያን ገዛሁበት" "በመሆኑም አሁንም የእኔ ነው ወደፊትም የራሴው ነው" ነበር ያሉት ታዲያ እንዲህ አይነት "እኔነት" የተጠናወታቸው አባት እንዴት ነው ይህንን የተለያየ አላማ እና አካሄድ ያለውን ሕብረተሰብ እመራለሁ ብለው የተነሱት፣ ሲሆን እንደ ጥንት አባቶቻችን በትህትና እና በፍቅር መጀመር ሲገባቸው ገና ሲጀምሩ በትዕቢት እና በማናለብኝነት የጀመሩት አቡነ ፋኑኤል በአዋሳ ሕዝብ ላይ ያደረሱትን በደል በዋሽንግተን ሕዝብ ላይ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል።

በዋሽንግተን አካባቢ በተለያዩ አስተዳደር ስር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት አሉ ከነዚህም ጥቂቶቹ
፩/ በእናት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር
፪/ በስተደኛው ሲኖዶስ አስተዳደር ያሉ
፫/ ያሉበገለልተኛ አስተዳደር ያሉ
፬/ ስደተኛውም ሲኖዶስ ወይም የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ የማይመሩ ነገር ግን በራሳቸው የቦርድ አስተዳደር ያሉ
፭/ በእናት ቤተ ክርስቲያን ያሉ ነገር ግን ያፓትሪያሪኩን ስም በጸሎት የማይጠሩ
፮/ በገለልተኛ አስተዳደር ያሉ ነገር ግን የባለቤቶቻቸውን የቅዱስ ሲኖዶስ ጥቂት አባላት ስር የሚተዳደሩ

እውነት ታዲያ አቡነ ፋኑኤልን መሪ አድርጎ ተቀብሎ የሚሰራ የትኛው ክፍል ነው እንደእርሳቸው አባባል የመጡት ለሁሉም ነው ብለዋል ታዲያ ይሳካላቸው ይሆን? ለጊዜው አሸንፈው የገቡት የራሴ ነው የግል ንብረቴ ነው ታክስ እከፍልበታለሁ ወይም መጦሪያ ቤቴ ነው በሚሉት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው፣ ቀጥሎስ የትኛውን አሸንፈው ወይም ብልጣ ብልጥ አባባላቸውን ተጠቅመው ማስተዳደር ይችሉ ይሆን? ጥያቄውን ለአናባቢ በመተው የደፊቱን አብረን ለመመልከት የዛሬውን በዚህ እያጠቃለልን በመቀጠል የአቡነ ፋኑኤልን አካሄድ ለአንባቢ እየተከታተልን ለማቅረብ ቃል እንገባለን።

ኢትዮጵያ ሀገራችንን፣ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ከአጽራረ ቤተክርስቲያን ይጠብቅልን አሜን


የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም። ዳን ፲፥፳፩


ቅዱስ ማለት ልዩ፥ ክቡር ማለት ነው፤ ሚካኤል ማለት ደግሞ «መኑ ከመ አምላክ፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው?» ማለት ነው። ሚካኤል የሚለው ስም ቃሉ የዕብራይስጥ ነው፤ ሚ - የሚለው «መኑ» ማለት ነው፥ ካ - የሚለው «ከመ» ማለት ሲሆን፥ ኤል - ማለት ደግሞ «አምላክ» ማለት ነው። ይህን ማለትም የቅዱስ ሚካኤልን ስም በጠራን ቊጥር የምንመሰክረው ስለ እግዚአብሔር ነው፤ በመሆኑም እግዚአብሔርን በባሕርይ የሚመስለው፥ በሥልጣንም የሚተካከለው፥ በምድርም በሰማይም እንደሌለ የሚናገር ልዩ፥ ክቡር ስም ነው። የነቢያት አለቃ ሙሴ ባሕረ ኤርትራን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን ያሻገረለትንና ፈርዖንን ከነሠራዊቱ ያሰጠመለትን አምላክ እግዚአብሔርን በመዝሙር ሲያመሰግን፥ «አቤቱ በአማልክት መካከል (በስም አማልክት ከሚባሉ፥ በስመ አማልክት ከሚጠሩ፥ አንድም አማልክት ዘበጸጋ ከተባሉ ከነቢያት ከካህናት መካከል) አንተን የሚመስል ማነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማነው?» ብሏል። ዘጸ ፲፭፥፲፩። ቅዱስ ዳዊትም፦ «አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፤» ብሏል። መዝ ፹፭፥፰። 
 ህዳር ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ሲመት በታላቅ ድምቀት  ታከብረዋለች ፡፡ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ ዳር 12 ቀን ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በኢዮር ባለችው በአራተኛይቷ ከተማ በሚኖሩት ኃይላት እና በአሥሩ ነገደ መላእክት ላይ አለቃ ሆኖ የተሾመበት ቀን ነው ፡፡እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ ገፍፎ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል፡፡(ይህን ሁለተኛውን ሹመት ያገኘው በሚያዚያ 2  እንደሆነ አክሲማሮስ በሚባለው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ አናገኛለን፡፡)

የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው ፡፡ ይህም እንደሆነ እንድንረዳ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለውን እስራኤል ዘሥጋን ሲራዳና ሲጠብቅ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን ፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ በኢያሪኮ ምድረ በዳ እንደተገለጠለት “… ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ ? አለው ፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ”(ኢያ.5፡13) ይለናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ ሲያወጣቸው ይመራቸው የነበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነበር ፡፡ ሹመቱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም በመሆኑ ስለ እነርሱ ዲያብሎስ ይዋጋው ፣ በጸሎትም ይራዳቸው ነበር ፡፡ ነገር ግን ኃጢአት ሠርተው ሲያገኛቸው ለእግዚአብሔር አድልቶ ኃጢአተኞችን ስለሚቀጣ እግዚአብሔር ሕዝቡን “በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት”(ዘጸ.23፡21)ብሎ አስጠንቅቋቸው ነበር ፡፡ ይህም ቅዱስ ሚካኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙን ያስረዳናል ፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሕዝበ እስራኤልን ይራዳቸው የነበረው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ አያረጋግጥም የሚል ካለ “መልአክ” የተባለው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ነቢዩ ዳንኤል በተላከ ጊዜ ገልጦልን እናገኛለን፡ሰይጣን ሠራዊቱን አሰማርቶ በአሕዛብ ነገሥታት እያደረ የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባሉ እስራኤልን ዘወትር በጦርነት ያስጨንቃቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ሲወድቁ ሲነሡ፥ ሲነቀሉ ሲተከሉ፥ ሲፈርሱ ሲገነቡ፥ ሲበተኑ ሲሰበሰቡ፥ ሲሰበሩ ሲጠገኑ ኖረዋል። በዚያ ዘመን መጋቤ ብሉይ ተብሎ የሚታወቀው ቅዱስ ሚካኤል ነው። እርሱም ዘወትር ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ሆኖ ሕዝቡን ይረዳቸው ነበር። ይኽንንም «ወደ አንተ የመጣሁት ለምን እንደሆነ ታውቃለህን? አሁንም የፋርስን አለቃ እዋጋው ዘንድ እመለሳለሁ፥ እኔም ስወጣ እነሆ የግሪኮች አለቃ ይመጣል። (ሰይጣን በግሪክ ንጉሥ አድሮ ሌላ ጦርነት ይጀምራል)። ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፥ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ (ከመላእክት አለቃ) ከሚካኤል በቀር የሚያጸናኝ የለም።» ዳን ፲፥፳፩ በማለት ቅዱስ ገብርኤል ለነቢዩ ለዳንኤል ነግሮታል። ቅዱስ ገብርኤል እንዲህ ካለ እኛስ ምን እንበል? 
የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፥ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት አይለየን አሜን።
  



Friday, November 18, 2011

‹‹አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን!››



ዘወትር ከአባታችን ሆይ ቀጥሎ በምናደርሰው ‹‹በሰላመ ገብርኤል›› በተሰኘው የጸሎት ክፍል ውስጥ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ በሥጋሽም ድንግል ነሽ›› የሚል የምስጋናና የምስክርነት ቃል ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በመልክዓ ማርያም ውስጥም ‹‹ሰላም ለሕሊናኪ ሐልዮ ሠናያት ልማዱ ወገቢረ ምሕረት መፍቅዱ›› ማለትም ‹‹ምሕረት ማድረግ ለሚወድ መልካም መልካሙን ማሰብ ልማዱ ለሆነ ሕሊናሽ ሰላም እላለሁ!›› የሚል የምስጋና ቃል አለ፡፡
የተአምረ ማርያም መቅድም ደግሞ የድንግል ማርያምን ሕሊና ከመላእክት ሕሊና ጋር ያስተያይና በልጦ ሲያገኘው በመደነቅ እንዲህ እያለ ያመሰግናል፡፡ ‹‹ሥጋዊ ነገር ከማሰብ መጠበቅ ከአዳም ልጆች ለማን ተሰጠው? ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ለመላእክት እንኳን አልተቻላቸውም፡፡ በቀደመው ወራት ያልተሰጣቸውን ሽተው በድለው ከሰማይ ወደ ምድር ወርደዋልና፡፡›› ከዚህም ጋር አያይዞ ‹‹የእመቤታችን ማርያም አሳብ እንደ አምላክ አሳብ ነው፡፡›› ይህም አሳብዋ ንጹሕና መልካም ብቻ መሆኑን ያስረዳናል፡:
እኛ ክርስቲያኖች ‹‹እግዚአብሔርን እንድንመስል›› ታዘናል፡፡ (1ጢሞ4.7-8፤ 1ቆሮ11.1) ይህም በመልክ አይደለም፡፡ በሥራና በአመለካከት እንጂ፡፡ እግዚአብሔርን በአመለካከት መምሰል የማይቻል ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔርን ምሰሉ አንባልም ነበር፡፡ በመልክ ስለመምሰል የሚናገር ቢሆን ኖሮ ደግሞ መልክን የሚፈጥረው ፈጣሪ ስለሆን ‹‹ምሰሉ›› አንባልም ነበር፡፡ የሚደንቅ ነው! እኛ ፈጣሪን በአሳብና በአመለካከት እንድንመስለው ታዘዝን፡፡ ድንግል ማርያም ግን መስላ ስለተገኘች ‹‹አሳብዋ እንደ አምላክ አሳብ ነው፡፡›› የሚል ምስክርነት ተሰጠላት፡፡
ቀደም ሲል ስለ ድንግል ማርያም ፍጹም የሕሊና ድንግልናና በጎነት ከአዋልድ መጻሕፍት ያስቀደምኩት ሆን ብዬ ነው፡፡ ይህንን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚደግፈው ማሳየት ያስፈልጋልና እነሆ!
ብዙ ሰዎች ስለ ድንግል ማርያም የሕሊና ንጽሕና ስንናገር በምን አውቃችው ነው? ለማለት ይዳዳቸዋል፡፡ በእርግጥ እኛ እንኳን የድንግል ማርያምን ሕሊና የኃጥአንንም ሕሊና የምናውቅበት ችሎታ የለንም፡፡ የጻድቃን ሕሊና ከኃጥአን ይልቅ እጅግ ይጠልቃል፡፡ የድንግል ማርያም ሕሊና ደግሞ ከሁሉ ይልቅ ጥልቅ ነው፡፡ ‹‹መንፈሳዊ ሰው በማንም አይመረመርም እርሱ ግን ሁሉን ይመረምራል›› ከተባለ ሰው ፍጹም መንፈሳዊት ድንግል ማርያምን ሊመረምር እንዴት ይችላል? (1ቆሮ2.15)
ታዲያ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ›› እያላችሁ ጠዋትና ማታ የምትዘምሩት የእርሷን ሐሳብ በምን አውቃችው? ለሚሉን መልሳችን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ድንግል ማርያም አሳብ ስለሚናገር ነው እንላቸዋለን፡፡ የት ቦታ ቢሉንም ቅዱስ ሉቃስ ሲጽፍ ‹‹ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው ብላ አሰበች›› ይላል፡፡ (ሉቃ1.29) ‹‹አሰበች›› ማለቱን ልብ በሉ፡፡ ይህን አለች ቢል ሰምቶ ነው፤ ይህን ሠራች ቢል አይቶ ነው ይባላል፡፡ ‹‹አሰበች›› ሲል ምን እንላለን? የክርስቲያኖች መልስ አንድ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ምን እንዳሰበች ገልጾለት ነው እንላለን፡፡ ሰይጣንና መናፍቃን የሚሉት አያጡምና ምናልባት ገምቶ ነው ሊሉ ይችላሉ፡፡ መቼም በዚህ አይሳቅም!!! መጸለይ ነው እንጂ፡፡
ይህ ብቻ አይደለም! በየርእሰ ጉዳዩ የድንግል ማርያም አሳብ ምን እንደሚመስል መንፈስ ቅዱስ ሲገልጥ ኖሮአል፡፡ ከዚህ የተነሣ ወንጌላዊው ሉቃስ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ ‹‹ይህን ሁሉ ነገር በልቧ እያሰበች ትጠብቀው ነበር፡፡›› ሲል መስክሯል፡፡ (ሉቃ2.19፤ ሉቃ2.51) መንፈስ ቅዱስ በልቧ ያለውን ካልገለጠለት ‹‹በልቧ እያሰበች ትጠብቀው ነበር›› እያለ ሊናገር እንዴት ደፈረ? በሰው ልብ ያለውን ከመንፈስ ቅዱስና ከሰውዬው በቀር ማንም ሊያውቅ እንደማይችል ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎ የለምን? (1ቆሮ2.11)
ድንግል ማርያም በሕሊናዋ የዚህ ዓለም ምኞት አልነበራትም፡፡ እንኳን ኃጢአቱና ኃጢአት ያልሆነውም ሥጋዊ አኗኗር በልቧ አልነበረም፡፡ ይህም ማለት ‹‹አግብቼ ወልጄ መልካም እየሠራሁ ቤተሰቦቼን እየረዳሁ እኖራለሁ›› የሚለው አሳብና ምኞት በውስጧ አልነበረም፡፡ ይህም ፈጣራ ሳይሆን በቅዱስ ዳዊት የትንቢት ቃል ይታወቃል፡፡ ስለ እርሷ ‹‹ልጄ ሆይ ስሚ ጆሮሽን አዘንብዪ የእናትሽንና የአባትሽን ቤት እርሺ›› ብሏል፡፡ ምእመናን! አባቷ ዳዊት እረ ስሚኝ፣ ጆሮ ስጪኝ እያለ ለምኖ ሲያመሰግናት ስሙ!!
‹‹እርሺ›› ማለት ምን ማለት ነው? አታስቢ ማለት አይደለምን? የምትረሳውስ ምንድር ነው? የእናት የአባቷን ቤት ነው፡፡ ይህ ማለት የእናት የአባትሽን ቤት አትመኚ! እንደ እነርሱ አግብቼ፣ ወልጄ እኖራለሁ ብለሽ አታስቢ ማለት ነው፡፡ ልብ በሉ! ቅዱስ ዳዊት ነቢይ ነው፡፡ እርሷ ይህን ዓለም እንድትረሳ የመከራት እንዳይመስላችሁ፡፡ እንደምትረሳው አውቆ በፈሊጥ ትንቢት ተናገረ እንጂ፡፡ አነጋገሩ እኮ ‹‹አቤቱ ተነሥ›› እንደሚለው ዓይነት ትንቢት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ይህን ቃል ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ተናግሮታል፡፡ (መዝ131.8) ኢየሱስ ክርስቶስ ዳዊት ‹‹ተነሥ›› ስላለው የተነሣ ይመስላችኋል? እንደሚነሣ አውቆ ትንቢት መናገሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንዲሁ ‹‹እርሺ›› ቢልም እንደምትረሳው አውቆ ትንቢት ተናገረ እንጂ ያስረሳት ዳዊት አይደለም፡፡
ታዲያ እንዲህ ኃጢአትን ሁሉ የዘነጋ ሕሊና ለማን ተሰጠው? እንዲህ ያለ ንጽሕናንና ቅድስናን የማያመሰግን አንደበት እንደምን ያለ ነው? እንዴት ያለ በደል ነው? እንዴትስ ያለ ድፍረት ነው? በበደል የረከስን ስንሆን ኃጢአትም ነግሣብን ሳለ ራስን ከፍ ለማድረግ ላላፈርን ለኛ ወዮታ ይገባል! እንኳን ከኀልዮ ኃጢአት ከተግባሩም ላልሸሸን ለኛ ኀዘን ይገባል፡፡ ‹‹እርሷ እንደኛው ናት!›› የሚሉ አርሲሳን /መናፍቃን/ ቦታቸው የት ይሆን? ሰው ባለማወቁ መጥፋቱን አያውቅም፡፡ መሬታዊው ሰው ደረጃውን አላዋቀምና ለዚህ ስንፍናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምላሹ ምን ይሆን?
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ! ድንግል ማርያም መልአኩን ‹‹ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል›› አለችው፡፡ መልአኩ ‹‹እነሆ ትጸንሻለሽ›› ባላት ጊዜ ታዲያ ምን ብርቅ አለው? ‹‹ሴት ልጅ ጊዜዋ ሲደርስ ታገባለች፤ ትጸንሳለች›› ልትለው ትችል ነበር፡፡ እርሷ ግን ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል?›› አለችው፡፡ ይህም ጥያቄዋ የልቧን መታተም ያስረዳል፡፡ አንዲት ሴት ባል ባይታጭላትና ባታገባ እንኳን ትወልጃለሽ ስትባል ‹‹ይሆን ይሆናል›› ትላለች፡፡ ወንድ ግን በተፈጥሮው የሚወልደው እርሱ ስላልሆነ ትወልዳለህ ቢሉት ‹‹እንዴት ይሆናል?›› ይላል፡፡ የድንግል ማርያም ንግግር የሁለተኛውን ይመስላል፡፡ የወንድ መውለድ የማይጠበቅ ነገር እንደሆነ በእርሷ ዘንድ መውለድ የማታስበው ጉዳይ ነውና ‹‹እንዴት ይሆናል›› አለች፡፡
እንደዚሁም መልአኩን ‹‹ወንድ ስለማላውቅ›› ብላዋለች፡፡ ይህም ለወደፊት እንኳን ወንድ ላለማወቅ ሕሊናዋን የዘጋች መሆኗን ያስረዳል፡፡ አለማወቋም ጾታ የመለየትና ያለመለየት ጉዳይ አይደለም በግብር ነው እንጂ፡፡ ለዮሴፍ የታጨችው ለተቃርቦ ቢሆን ኖሮ ወንድ ስለማላውቅ ባለችው ጊዜ መልአኩም መልሶ ምነው ዮሴፍ አለ አይደል ሊላት በቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን መልአኩ እንደዘመናችን መናፍቃን አያስብምና የልቧን ንጽሕና አይቶ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን እንደምትወልድ ነገራት፡፡ ለማሳመንም ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም›› አላት እርሷም ነገሩን በጥንቃቄ መርምራ ስታበቃ ‹‹ይደረግልኝ›› ብላ በትሕትና ቃሉን ተቀበለችው፡፡ ያን ጊዜ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ የዕለት ጽንስ ሆኖ በማኅፀኗ አደረ፡፡


የሕሊናዋ ነገር እንደዚህ ከሆነ ቅዱስ ዳዊት ‹‹አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን!›› በማለት ሰው እንዳይገድል እጁን ከደም የከለከለችውን ሴት አእምሮ ካመሰገነ እኛ ክርስቲያኖች ድንግል ማርያም በቀን ስንት ጊዜ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ›› እያልን ልናመሰግናት ይገባን ይሆን? (1ሳሙ25.33)

by
ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ

Thursday, November 17, 2011

በአቡነ ፋኑኤል ሥርዓት አልበኝነት የተቃውሞ ሕዝባዊ ጥሪ ለመላው ዓለም



ለዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ!

አቡነ ፋኑኤል በገጠማቸው ቀውስ እንዳዘኑ!
 ከትላንት በስቲያ ሰኞ ከቀትር በፊት አቡነ ፋኑኤል በድብቅ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ገብተው ማደራቸው ተዘግቧል፥ በእለት በገቡበት ዕለት ከፍተኛ ተቃውሞ እንደሚገጥማቸው ተገምቶ ስለነበር ቀድመው ለሰዎች ሐሙስ ብለው በሀሰት ፕሮፓጋንዳ አስነግረው ነገር ግን እሳቸው ሰኞ ከእኩለ ቀን በፊት ማንም ሳይሰማ ወደ ከተማው ገብተው አድረዋል። በዚሁ እለት በቨርጂኒያው አየር ማረፊያ እንደደረሱ አጠገባቸው ሆነው እርሳቸውን እና አላማቸውን በመደገፍ የሚታወቁት የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካሕናት እንዲሁም ከአካባቢው ካሕናት እነ ቀሲስ ታደሰ ሲሳይ እና በቀሲስ ኢስሃቅ አማካኝነት ከአየር ማረፊያ ተቀብለዋቸው በቀጥታ በደቡብ ምዕራብ ዋሽንግተን  ወደሚገኘው የደብረ ምሕረት ገንዘብ ያዥ ወደ ሆነው ሰው መኖሪያው ቤት በቀጥታ አምርተው በዛው ቀናትን ለማሳለፍ ተገድደዋል። ባለፈው እንደዘገብነው በዚህ ጉዞዋቸው በጋሻውን ይዘው ለመምጣት ብዙ ጥረቶችን ለማድረግ ቢሞክሩም የተሳካላቸው አይመስልም፣ ነገር ግን እርሱን ለማምጣት የሚቻላቸውን እንደሚያደርጉም ቅዱስ ፓትሪያሪኩም ቃል እንደገቡላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አንድ የአካባቢው ክርስቲያን በዛሬው ዕለት በላከልን መልዕክት እንደሚያስረዳን በመጪው እሁድ የሚከበረውን የቅዱስ ሚካኤልን በዓል ለማክበር የመጡት አቡነ ፋኑኤል ከባድ ተቃውሞ እንደሚገጥማቸው ከወዲሁ በመረዳት የደብሩ የቦርዱ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው የሚከተሉትን መመሪያዎች አስተላልፈዋል

፩ኛ/ በክብረ በዓሉ ቀን ማንም ሰው መኪናውን በጊቢው ውስጥ እንዳያቆም (ለጸጥታ ስለማይመች)
፪ኛ/ ከአካባቢው የፓሊስ ቢሮ ከሁለት እስከ አራት የፓሊስ ሰራዊት በቦታው ተገኝቶ ክብረ በዓሉን እንዳይታወክ እንዲቆጣጠሩ
፫ኛ/ አቡኑም ምንም አይነት ንግግር እንዳያደርጉ
፬ኛ/ ቢቻል በዑደቱም ላይ ባይኖሩ የሚሉትን መመሪያዎች አስተላልፏል።

ከዚህ የቦርዱ መመሪያ እንደምንረዳው በደብረ ምሕረት አካባቢ አቡኑ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ አለመረጋጋት እና መሸበር እንዳለ ከአካባቢው መረጃውን ያደረሱን ክፍሎች ያስረዳሉ። በተያያዘ ዜና በዚሁ እሑድ በሚደረገው የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል ላይ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ተቃውሞ እንደሚደረግ ከዚህ ጋር አያይዘው ገልጸውልናል፣ በመጪው እሑድ ከፍተኛ ትዕይንቱን በማዘጋጀት ላይ ያሉት ወገኖቻችን እንዳስረዱን ከሆነ አላማቸውን በግልጽ አስቀምጠው የአቡነ ፋኑኤልን አስተዳደርም ሆነ ውክልና አንቀበልም። ልክ እንደ ከዚህ በፊቱ በተለያዩ የሀገራችን የኢትዮጵያ ክፍሎች ተመድበው ሥራ ከመስራት ይልቅ መከፋፈልንን እና ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት ሥራ ላይ ተሰማርተው አብሮ ለብዙ ዘመን የኖረውን ሕብረተሰብ ለያይተው ሲያበቁ እርሳቸውም ከሀገረ ስብከታቸው በሕዝቡ ብሶት እና በቅዱስ ገብረኤል ረዳትነት ከቦታቸው ተነስተዋል። እዛ በነበሩባቸው ጊዚያት አቡነ ፋኑኤል "እኔ አሜሪካው ነኝ ምንም ልታደርጉኝ አትችሉም" እያሉ በደሃው ሕዝብ ላይ ሲንቀባረሩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፣ ሆኖም በአሁን ሰዓት ቤተ ክርስቲያንንም ወክለው ይሁን በገንዘብ ገዝተውት ወደ ዋሺንግተን አመጣታቸውንም ሆነ ውክልናቸውን እንደማይቀሉ አስታውቀው፣ ጥያቄያቸውንም በአቸኳይ የማይመልሱ ከሆነ ማንኛውንም እርምጃ ለማድረስ ማንኛውንም ዝግጅት አድርገው ለዚህም ደግሞ በማንኛውም መልኩ የገንዘብም ሆነ የሰው ሃይል በሚገባ ስላላቸው በሕግም ይሁን ከሕግ ውጪ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጅታቸውን እና ቁርጠኝነታቸውን አሳውቀውናል።

በቤተ ክርስቲያኑ አካባቢም ምዕመናኑ፣ አገልጋዮች ካሕናት እንዲሁም ዲያቆናት ለሁለት እነደተከፈሉ ይነገራል። በአገልጋይ ሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች በኩል ባለፈው እሑድ ተሰባስበው ግማሹ የሰንበት ት/ቤት ከአየር ማረፊያ ሄደን መቀበል እና ማጀብ ይኖርብናል ሲሉ እንዲሁ ግማሹ ደግሞ አይደለም አየር ማረፊያ ሄደን ልንቀበላቸው እዚህ መቀመጥ የለባቸውም፣ እስከ ዛሬ ድረስ በእንግድነት ነው ተቀብለናቸው ያስተናገድናቸው ከዚህ በኃላ ግን ሥልጣኑን በምንም መንገድ ያግኙት እኛ ከዚህ በኃላ ሊወክሉንም እንደ አባት ልንቀበላቸውም አንችልም በማለት አማረው ተናግረዋል። በአገልካይ ካሕናትም በኩል ገሚሶቹ ምን ችግር አለው ተቀብለን ማገልገል ነው እንደውም እስከ ዛሬ ድረስም የሳቸውን ሥም ነው ጠርተን ሥርዓተ ቅዳሴውንም የምንፈጽመው አሁን ደግሞ ሕጋዊ ወኪል ስለሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ስለላካቸው መቀበል የግዴታችን ነው በማለት በብልጥነት ለማስቀመጥ ይሞክራሉ። ከፊሎቹ ደግሞ የሰንበት ት/ቤቱ ዓይነት ተመሳሳይ አቋም ይዘው እስካሁን ስማቸውን የምንጠራው ከሰሩት ሥራ አንፃር ነው እንዲሁም ባለቤትነቱ የርሳቸው ስለሆነ ነው ይሁንና ከዚህ በኃላ እርሳቸውን እንደ ዋሽንግተን ዲሲ እና የምዕራብ ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብንቀበል ፓትሪያሪኩን የመቀበል እና በሥርዓተ ጸሎቱ ላይ የመጥራት ግዴታ ሊመጣብን ይችላል፥ ያማለት ደግሞ ሕዝባችንን በጣም ስለሚያስቆጣው ይሄኛው አካሄድ ሊያዋጣን አይችልም በሚል ከፍተኛ ተቋውሟቸውን ግልጸዋል። እንደ መረጃ አቀባያችን አገላለጽ ከሆነ በማንኛውም መልኩ የደብረ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ከዚህ በኃላ ለሁለት ወይም ለሦስት ቦታ የሚከፋፍለው መንገድ እንዳለ በግልጽ አሳይቷል በመሆኑም የአቡነ ፋኑኤል አመጣጣ በማንኛውም መመዘኛ የአካባቢውን ሕዝብ ቀርቶ የደብረ ምሕረትን ሕዝበ ክርስቲያን እንኳ ሊወክሉ እንደማይችሉ ከወዲሁ ተፈርቷል፣ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኗ ሕልውና ያሰጋቸው ምዕመናንም የፊርማ ማሰባሰቢያ እና ደብዳቤ አዘጋጅተው ለወከላቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ በአስቸኳይ እንዲነሱልን ሲሉ ደብዳቤዎችን እና የፊርማ ማሰባሰቡን ሥራ ከወዲሁ እንደጀመሩት ከወዲሁ ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪ በዚሁ በመጨው እሑድ ህዳር ፲ ቀን (Nov. 20, 2011) ማለትም የቅዱስ ሚካኤል በዓለ ንግስ እለት ታላቅ የሆነ ሕዝባዊ ተቃውሞ እንደሚያደርጉ እና አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት አድርገው እንደጨረሱ እና የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ እርዳታ እና ትብብር በመጠየቅ አስፈላጊውን ትብብር እንዲደረግላቸው ከወዲሁ ጥሪ እንድናደርግላቸው ከመልዕክቱ ጋር ተያይዞ ደርሶናል። በዚህ ሕዝባዊ ተቃውሞ ላይ እያንዳንዱ ሀገር ወዳድ እና የኦርቶዶክሳዊ ቤተ ክርስቲያኑ ሥርዓት ግድ የሚለው ሁሉ የዚህ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተካፋይ እንዲሆን ከወደሁ አዘጋጆቹ አስቀድመው ጥሪያቸውን አድርሰውልናል። የዚህ ዝግጅት አስተባባሪዎች እንደገለጹልን ከሆነ አቡነ ፋኑኤል እና ተባባሪዎቻቸው ይሄንን ክብረ በዓል ተጠቅመው የቪዲዮ ቀራጭ ባለሙያ ግምቱ $2000.00 ብር ከፍለው በቪዲዮ አስቀርጸው እና አቀናብረው ልክ ሕዝቡ እንደተቀበላቸው አስመስለው "ሕዝቡ ተቀብሎናል ሃሳብ አይግባችሁ" ብለው ፕሮፓጋንዳቸውን ለመሥራት እና ወደ ኢትዮጵያም ለመላክ ቅድመ ዝግጅትም እያደረጉ እንደሆነ ከወዲሁ ለመረዳት ተችሏል። አባ ፋኑኤል እና ግብረ አበሮቻቸው እንዲህ ዓይነት ትውልድን የማያንጽ ሥራ እየሰሩ፣ ጽድቅ ያይደለ ተንኮል፣ እውነት ያይደለ ሐሰት የተሞላበት እየሰሩ እንደገና ልክ በጣም ትጉህ የሆኑ ዓይነት መለስ ቀለስ በማለት ሰውን ለማወዳበድ የሚያደርጉትን ሤራ እና ተንኮል ከወዲሁ ልንገነዘብ ያስፈልጋል እንላለን። አሁንም ሥራ ሰርተናል ብለው ለማለት እንዲህ አይነት ድራማ በማን ላይ የሠሩ እንደሆነ ያልተገነዘቡት እነዚህ ክፍሎች ከተንኮል ይልቅ፣ ትህትና፣ ከበደል ይልቅ ፍቅርን ቢማሩ እና ቢያስተምሩ ይሻላል እንላለን። እነዚህን ሁሉ የተንኮል እና የድራማ ዝግጅቶችን ለመሥራት መዘጋጀታቸው በራሱ እራሳቸውን እና ሕሊናቸውን እያታለሉ ጊዜያቸውን ለመፍጀት ያሰቡ አባት እንጂ ለሥራ የመጡ አባት እንዳልሆኑ ይሄ ሥራቸው እራሱ ትልቅ ምስክር ነው በማለት አዘጋጆቹ በምሬት ገልጸውልናል።

ቸር ወሬ ያሰማን፣ አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ያስታግስልን አሜን
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም. የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተቃውሞ ሰልፍ እይታዎች

 ቪሲዲውን ለመመልከት እዚህ ይጫኑ
ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም. የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በአዲስ አበባ መንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተሐድሶ መናፍቃን ላይ ያደረጉትን የተቃውሞ ሰልፍ የሚያሳይ የ 20 ደቂቃ ቪሲዲ ለዛሬ አቅርበንላችኋል
በሰልፉ ላይ በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ከሚገኙ የ131 ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ያላቸውን የደንብ ልብስ(ዩኒፎርም)እና ነጠላ በመልበስ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምቱ ጉባዔው በተሐድሶ መናፍቃን ላይ እርምጃ እንዲወስድ ሲያሳስቡ ይታያል፡፡ ወጣት የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎቹ ተቃውሞአቸውን በአደባባይ ከማሰማታቸው በፊት ቀደም ባሉት ጊዜያት መዋቅራቸውን ጠብቀው ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትና ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት የተሐድሶ መናፍቃንን ማንነት የሚያጋልጥ ባለ 261 ገጽ የጽሑፍ ሰነድና 14 የምስል እና የድምጽ(VCD) ሰነድ በማስረጃነት ማቅረባቸው ቢታወቅም አደባባይ ለመውጣት እነዳላሰቡ ሆኖም ግን እነ በጋሻው፣ትዝታው፣አሰግድ፣ናትናኤል፣ያሬድና ሌሎችም የተሐድሶ ሎሌዎች ስማችን ጠፋ፣ መድረክ ተከለከልን፣ ተሐድሶ የሚባል የለም ፣ወዘተ….በማለት በለመዱት የግራ ዐይን የአዞ እንባቸው ሕዝቡን ለማሳሳት ሰልፍ እንወጣለን ብለው በማወጃቸው ምክንያት ወጥተው ተቃውሞአቸውን እንዳሰሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቪሲዲው፦
• “የዘማሪ” ትዝታው ሳሙኤልን መደብደብና መዋከብ ኋላም በድንጋጤ ጥግ ላይ ተደብቆ ጥርሱን እየነከሰ መንቀጥቀጥን፣
• የተሐድሶ መናፍቅ አሰግድ ሳህሉን ተንኮሳና መንቀዥቀዥ ኋላም መደንገጥና መሸማቀቅን፣
• የ“ዘማሪት” ቅድስት ምትኩንና “ዘማሪት” የትምወርቅን ድፍረትን፣
• የመናፍቁ ናትናኤል ታምራት በፍርሃት ታጥሮና ጥግ ይዞ መታየትን፣
• የ“መምህር” ተረፈን የመሃይም ድፍረትና በኋላም ቅሌትና ውርደት፣
• የሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴንና የቅ/ማርያም ገዳም አስተዳዳሪ አላዋቂነትና አድርባይነትን፣
• የአዲስ አበባን ሰንበት ት/ቤቶች በወኔ የታጀበ ጠንካራና የተደራጀ ተቃውሞን፣
• የቅዱስ ፓትርያርኩን ብስጭትና ወገንተኛነት፣
• የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊሶችን የተረጋጋ፣ሕጋዊና ሰላማዊ የጸጥታ ማስተባበር ሥራን፣
• የአዲስ አበባ ምዕመናንን እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ቅናት ወዘተ…..በአንጻሩ ደግሞ የተሐድሶ መናፍቃንን ድፍረትና አይን አውጣነት ያሳያል፡፡
• የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ቤተ ክርስቲያናችን በተሐድሶ መናፍቃን አትወረርም የሚል አገር አቀፍ ብሎም ዓለም አቀፍ የሆነ አጀንዳ ይዘው ታይተዋል፤
ቪሲዲው ከ“ዘማሪያኑ” እነ ትዝታው ሳሙኤል፣የትምወርቅ፣ቅድስት ምትኩ፣ምርትነሽ ጥላሁን፣ሃብታሙ ሽብሩ፣ሐዋዝ ተገኝ፣…..ከ“መምህራን” ናትናኤል ታምራት፣አሰግድ ሣህሉ፣ተረፈ፣ጋሻዬ መላኩ፣ስንታየሁ፣በፈቃዱ፣ታሪኩ አበራ….ነበሩበት፡፡የአዲስ አበባ ምዕመናን “ፍንዳታ”እያሉ የሚጠሯቸው የመነኩሴ ቆብ ያጠለቁ የተሐድሶ መነኮሳትም ነበሩበት፡፡
እነበጋሻውና ያሬድ አደመ ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው ማስተባበርን መርጠዋል፡፡ማንነታቸው እንዳይታወቅ ፊታቸውን በሰፊ መነጽር ለመሸፈን የሞካክሩ ኮረዳዎችም በሰልፉ ነበሩበት
ባአጠቃለይ ቪሲዲው አንድ ሰዓት ያህል ቢፈጅም እኛ ግን አሳጥረን በ20 ደቂቃ አቅርበንላችኋል። ሙሉውን ቪሲዲ በዚሁ  በደቂቀ ናቡቴ ጦማረ መድረክ በቅርቡ የምንለቀው ይሆናል። ቪሲዲው ኤዲት ስለሚጎድለውና ስለ ድምፁ ጥራት ይቅርታ እንጠይቃለን። 
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ አሜን።

Friday, November 4, 2011

የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ 12ኛ ቀን ስብሰባ ዋና ዋና ዜናዎች



 (ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 24/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 4/2011)፦
  • አቡነ ፋኑኤል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በሽምግልና በመጠቀም በዋሽንግተን ዲሲ እና በካሊፎርኒያ የሚጠብቃቸውን መሬት አንቀጥቅጥ ተቃውሞ ለማብረድ እና የአሜሪካ ሹመታቸውን ለማደላደል እየተጣጣሩ ነው፤
  • ቅ/ሲኖዶስ በመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ችግሮች ላይ የቀረበው የዳሰሳ ምልከታ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሚመራ የባለሞያዎች ኮሚቴ እንዲገመገም ወሰነ፤
v  በኤፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የፌዴራል መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም፣ ለማደራጀት እና ለማጠናከር የተዘጋጀውን ዐዋጅ ረቂቅ መርምሮ በማስተካከል በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሕግ ዕውቅና እንዲያገኝ ይላክ ዘንድ መርቷል፤ መንፈሳዊ ፍ/ቤቶቹ የመንግሥትን የፍትሕ አካላት ላጨናነቁት የቤተ ክህነት ጉዳዮች እፎይታ እንደሚሰጡ ተስፋ ተደርጓል፤
v  የጋብቻ፣ ፍቺ፣ ቀለብ አወሳሰን፣ አካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ሞግዚትነትና በቤተሰብ ተዛምዶ ላይ የሚነሡ ጥያቄዎች፣ የውርስ፣ የኑዛዜና የስጦታ ጉዳዮች፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ ከላይ በተገለጹት ጉዳዮች ላይ በሚቀርቡ ክሶች ኪሳራ መወሰን የፍ/ቤቶቹ የወል ዳኝነት ሥልጣን ክልል የሚሸፈኑ ናቸው፡፡
v  በፍ/ቤቶች ጉዳያቸው የሚታየው በቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ሥርዐት በፍ/ቤቶቹ ለመዳኘት ተስማምተው በፈቃዳቸው የቀረቡ አገልጋዮች እና ምእመናን ናቸው፡፡
v  ፍ/ቤቶቹ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ የሚቋቋሙ ሲሆን መሪዎቹ ‹‹ርእሰ ፍትሕ›› የሚል ማዕርግ ይሰጣቸዋል፤
  • ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በአጀንዳ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ተጠምደዋል - አቡነ ሳሙኤልን ስለ ወነጀሉበት ክስ፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ስለ ማሻሻል እና ስለ ተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጉዳይ ቀደም ሲል በምልአተ ጉባኤው ውድቅ የተደረጉባቸውን ጉዳዮች በተለያየ ቀለም መልሰው ቢያነሡም ዳግመኛ ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል፤
  • አባ ሰረቀ ‹‹ከሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ዋና ሐላፊነታቸው እንዲነሡ በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተላለፈውን ውሳኔ ለመቃወም›› በሚል የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሠልጣኞች በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት መካከል የተቃውሞ ፊርማ እያሰባሰቡ ነው፤ የደቀ መዛሙርቱን የጋራ ጥያቄዎች ለሽፋንነት ይጠቀማሉ የተባሉት ተቃዋሚዎቹ በአባ ሰረቀ ላይ በተላለፈው ውሳኔ ሁነኛ ሚና ተጫውተዋል ባሏቸው ማረፊያ ቤታቸው በቅጽሩ በሚገኘው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና ሌሎች በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይም እንዳነጣጠሩ ተጠቁሟል፤ እንቅስቃሴውን አባ ሱራፌል የተባሉት የፓትርያርኩ ዘመድ እና ከአራት ያላነሱ “የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ጭፍሮች ናቸው” የሚባሉ (ዲ.ን አብርሃም ይገዙ - ከነገሌ ቦረና፣ ዲ.ን በረከት ታደሰ - ከአሰበ ተፈሪ፣ ዲ.ን መስፍን ታዬ - ከሐዋሳ፣ ዲ.ን አሳምነው ዐብዩ - ከአምቦ የመጡ እና በልደታ አካባቢ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መደበኛ ሥልጠና የወሰዱ) እና ዲ.ን መንግሥቱ - ከባሕር ዳር የተመደበ ያስተባብሩታል፤ ፓትርያርኩ አጋጣሚውን በመጠቀም የአባ ሰረቀን ጉዳይ መልሰው ሊያነሡ እንደሚችሉ ተገምቷል፤
  • በ17ኛ ተራ ቁጥር በተመለከተው ልዩ ልዩ አጀንዳ ሥር ፓትርያርኩ ለውይይት ያቀረቡትና “ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ላይ ከሐዋሳ መጥተዋል በተባሉ ሰዎች ቀርቧል የተባለውን ክስ” ቅ/ሲኖዶሱ ውድቅ አድርጎታል፣      
  • በተመሳሳይ “በልዩ ልዩ” ሥር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ አክሱም ጽዮን ማርያም፣ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም እና ቅዱስ ላሊበላ ደብር በጳጳሳት እንዲመሩ ያቀረቡት ሐሳብ በምልአተ ጉባኤው አባላት ተቀባይነት አላገኘም፤ በዚሁ አጀንዳ ሥር የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ደርበው የሚመሩት ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀውስጦስ የመልቀቂያ ጥያቄ ያቀርባሉ ተብሏል፤
  • ከወትሮው በተለየ ለተከታታይ 13ኛ ቀን ቀጥሎ የሚገኘው የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቃለ ጉባኤዎቹንና የስብሰባውን መግለጫ ረቂቅ  በመናበብ ይፈራረማል፤ የምልአተ ጉባኤው ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ ነው።

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Tuesday, October 25, 2011

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተጀመረ


 የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአጀንዳ ረቂቅ ላይ ሲወያይ ዋለ 

  • በኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እና በዕርቀ ሰላም ጉዳይ አጀንዳ ላይ ልዩነቶች አሉ 
  • የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እና ማኅበረ ቅዱሳን ከማ/መምሪያው ጋራ ስላለው ግንኙነት የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት በአጀንዳው ረቂቅ ውስጥ ተካተዋል 
  • “ያረፉ ብፁዓን አበው ሀብት እና ንብረት ወራሾች ነን” በሚሉ ሐሰተኞች ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እየተቸገረ መሆኑ ተገለጸ
  • “በኤጲስ ቆጶሳት ሹመት የካህናት እና የምእመናን ተሳትፎ ይጨመርበት፤ በጳጳሳት ሀብት እና ንብረት ውርስ ጉዳይ የቀድሞው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይመለስ” (የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ)፤
  • “ዛሬ ገንዘብም ጭምር የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት እንጅ ቅኔ ብቻ የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት የትንቷ ደሃ ቤተ ክርስቲያን የለችም” (ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ)፤
 (ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 11/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 22/2011)፦ ስምንት አባላት ያሉትን የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ በመምረጥ ዛሬ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2004 ጠዋት የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እንዲያዙላቸው ካቀረቧቸው የአጀንዳ ረቂቆች መካከል በተጨማሪ ኤጶስ ቆጶሳት ሹመት እና የኮሚቴው አባላት ካቀረቧቸው አጀንዳዎች አንዱ በሆነው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዕርቀ ሰላም ጉዳይ ላይ ሲወያይ ውሏል፤ በፓትርያርኩ እና በተቀሩት የጉባኤው አባላት መካከል በታየው የአቋም ልዩነት ምክንያት ውሳኔ ሳይደረግበትም ለነገ አድሯል፡፡

የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ አባላት ሆነው የተመረጡት ስምንት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡- ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘካናዳ እና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ናቸው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በ2003 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ 30 ያህል ኤጲስ ቆጶሳትን መሾምን አስመልክቶ የነበራቸውን አቋም አጠናክረው ቀርበዋል፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱም ከሹመቱ አስቀድሞ የኤጲስ ቆጶሳቱሿሿም በተመለከተ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የታዘዘውን ከማስጠበቅ እና በዚህም መንፈስ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ከማጠናከር እንዲሁም ከተሚ ዕጩዎቹ አኳያ የተገቢነት እና ወቅታዊነት ጥያቄ በማንሣት ከስምምነት ሊደረስ ባለመቻሉ አጀንዳው ለነገ አድሯል፡፡

ከትናንት በስቲያ ለኅትመት የዋለው የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ በበኩሉ፣ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በጳጳሳት ሀብት እና ንብረት ውርስ እና በጳጳሳት ምርጫ ላይ ትኩረት በመስጠት መክሮ እና ዘክሮ ከሞት በፊትም ሆነ ከሞት በኋላ በብፁዓን አባቶች ላይ የሚከሠቱ ችግሮች እንዳይኖሩ የቀድሞውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የጠበቀ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ጋዜጣው በመስከረም እና ጥቅምት 2004 ዓ.ም እትሙ ባሰፈረው ርእሰ አንቀጽ፣ ከቀድሞዎቹ አባቶቻችን ሲደረግ በቆየውና ዛሬም ድረስ በቀጠለው ጥረት “ቤተ ክርስቲያን ከድህነት መሥመር ወጥታ ካህናት አገልጋዮቿ በሞያቸውና በአገልግሎታቸው መጠን ክፍያ የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠሩን” ያውጃል፡፡ በዚህም መሠረት አበው ጳጳሳት በወርሐዊ ደመወዝ፣ በትራንስፖርት፣ በሕክምና፣ በመኖሪያ (ማረፊያ) ቤት፣ በማዕድ አገልግሎት ሳይቀር የትናንቱ ሰቀቀን እንደቀረላቸው በመዘርዝር በሞተ ዕረፍት በሚለዩበት ወቅት ያስታመመቻቸው፣ የተንከባከበቻቸው ቤተ ክርስቲያን ሳለች “ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን ወራሾች እኛ ነን” እያሉ የሐሰት የውርስ ሰነድ ይዘው የሚመጡ ቤተሰብ ተብዬዎች በሚያቀርቡት አቤቱታ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና አስተዳደሩ ፍትሕ ለመስጠት እየተቸገሩ መሆናቸውን አትቷል፤ ውርሱ ይገባናል ባዮቹ ይህን የሐሰት ውርስ ሰነድ ይዘው ወደየፍርድ ቤቶች በመሄድ የብፁዓን አባቶቻችንንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በማጉደፍ ላይ እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡

ርእሰ አንቀጹ የችግሩ መንሥኤ በቅርቡ በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን አበው በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበት ጊዜ ገንዘባቸውንና ያፈሩትን ንብረት ሁሉ የሚያሳድጓቸው እጓለማውታዎችና የሚረዷቸው ችግረኞች ቤተሰቦች እንዲወርሱ በሥርዋጽ በገባው ቃል የተላለፈው ድንጋጌ መሆኑን ገልጧል፡፡ ስለሆነም የብፁዓን አባቶችንም ሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ለመጠበቅ ሲባል የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ድንጋጌውን እንደገና እንዲፈትሸው ጠይቋል፡፡

ጵጵስና የሚሾመውን አባት መምረጥ እና መሾም የሚገባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ካህናትና ምእመናንም “አክዮስ አክዮስ ማለት ይደልዎ ይደልዎ” ብለው መምረጥና መሾም እንደሚገባቸው ያስታወሰው ርእሰ አንቀጹ፣ ይህን በማድረግ  ሁለንተናዊ ብቃት ያለው ወይም ነውርና ነቀፋ የሌለው አባት መምረጥና መሾም እንደሚቻል አስገንዝቧል፡፡
/ሙሉውን የርእሰ አንቀጹን ይዘት ከዚህ በታች ይመልከቱ/
+ + +
የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ
አስታማሚ ቤተ ክርስቲያን ወራሽ ቤተሰብ
/ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ 57ኛ ዓመት ቁጥር 122፤ መስከረም እና ጥቅምት 2004 ዓ.ም/
ከዛሬ ዐርባ ዓመት በፊት በነበረው የዘውድ መንግሥት ሥርዐት ጥንታዊቷ፣ ታሪካዊቷና ብሔራዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት የጠበቀ ግንኙነትና ትስስር ነበራቸው፡፡በየዘመናቱ የሚነግሡትን ነገሥታት ሁሉ ቀብታ የምታነግሥ እሷ ነበረች፡፡ ከዚህም የተነሣ ነገሥታቱም ሆኑ መሳፍንቱ ለቤተ ክርስቲያናችን ይሰጡት የነበረው አክብሮት፣ ያደርጉት የነበረው ድጋፍ፣ ጥበቃና ክብካቤ እጅግ በጣም የተለየ ነበር፡፡ ከግብጻውያን የባርነት ቀንበር ተላቅቃ መንፈሳዊ ነጻነቷን ሙሉ በሙሉ እንድትጎናጸፍ የከፈሉትም መሥዋዕትነት በዋጋ የሚተመን አልነበረም፡፡ የምትጠቀምበት ርስት ጉልት ያደረጉ ከመሆናቸውም በላይ በሕገ መንግሥታቸውም ከፍተኛ ሥፍራ ነበራት፡፡

ከዚህም ሌላ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች በሞያቸው፣ በቅድስናቸው እና በአገልግሎታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በካህናትና በምእመናን ከፍተኛ ድምፅ ተመርጠው ሢመተ ጵጵስና በሚቀበሉበት ጊዜ ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን የሚፈጽሙባቸው መኪናዎች፣ የእጅ መስቀሎችና አርዌ ብርቶች፣ ልብሰ ተክህኖም ጭምር ይሰጧቸው ነበር፤ ወርሐዊ ደመወዛቸውንም የሚያገኙት ከመንግሥት ነበር፤ ለጠቅላይ ቤተ ክህነትም መንግሥት መጠነኛ የገንዘብ ድጎማ ያደርግ ነበር፡፡ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲሦ መንግሥት አላት”እየተባለ ይነገር የነበረውም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡

ይህም በመሆኑ ጳጳሳቱም ሆኑ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ካህናት በሙሉ በጸሎተ ቅዳሴያቸው ዘወትር ወደ ፈጣሪያቸው በሚያቀርቡት ጸሎት “ዕቀብ ንግሦ ወሠራዊቶ ለንጉሥነ እገሌ፤ አግርር ፀሮ ታህተ እገሪሁ” ማለት “ንጉሥን ከነሠራዊቱ ጠብቀው፤ ጠላቶቹንም ከእግሩ ሥር አስገዛለት” እያሉ በመጸለይ አያሌ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡ ደብተሮቹ ወይም ያሬዳውያን መዘምራኑም በበኩላቸው በያሬዳዊ ዝማሬያቸውና በቅኔያቸው ጣልቃ እያስገቡ ነገሥታቱን ሲያወድሷቸው፣ ሲያሞግሷቸውና ንጉሣዊ ተግባራቸውን በማጋነን ሲገልጡላቸው ይስተዋሉ ነበር፡፡

ከዚህም በላይ እንደተገለጸው ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት የመንግሥት ጥገኛ ሆና ራሷን ሳትችል መኖሯ በሁሉም ዘንድ የተሰወረ ምሥጢር አይደለም፤ በዘመነ ደርግ የደረሰባትን ከፍተኛ ተጽዕኖም ታሪክ አይዘነጋውም፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ተረኛ ሆኖ አገሪቱን መምራትና ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ ግን የተወረሱት ቦታዎች፣ ቤቶችና ንብረቶች ሁሉ ተመልሰውላት ራሷን በራሷ እንድትመራና እንድታስተዳድር መደረጉ ትጋትንና ጥንካሬን እንድታገኝ በእጅጉ ረድቷል፡፡

ስለዚህ በአሁኑ ወቅት የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነጻ የወጣች እንጅ እንደ ትላንቱ ጥገኛ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡፡ አሁን በሚመሯት ዓለም አቀፍ አባት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የበላይ መሪነት፣ በልጆቿ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አስተዳዳሪነት የምትመራ ቤተ ክርስቲያን እንጅ እንደ ትላንቱ ቋንቋዋን የማያውቅ ምእመን ከቤተ መንግሥት ተልኮ የሚያስተዳድራት ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡

በኢኮኖሚውም አኳያ ያለፉት ብፁዓን አባቶቿና አገልጋዮቿ ካህናት ጦም ውለው ጦም አድረው ለዝንተ ዓለም በአክፍሎት እየኖሩ ያገለግሏት የነበረችው የትላንቷ ደሃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በድህነት መስመር አትገኝም፡፡ “አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው” እንዲሉ እነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን የመሳሰሉት አርቆ አስተዋዮች አባቶቿ በሰበካ ጉባኤ አደራጅተዋት ስለ አለፉ ዛሬ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ሆኑ አገልጋዮቿ ካህናት ሁሉ በሞያቸውና በአገልግሎታቸው መጠን ክፍያ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ዛሬ ገንዘብም ጭምር የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት እንጅ ቅኔ ብቻ የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት የትላንቷ ደሃ ቤተ ክርስቲያን የለችም፡፡ የትላንቱን አስተንትኖና ከፍተኛ ለውጡን በውል ተገንዝቦ ተመስገን ለማለት እንዲችል የዛሬው አገልጋይ እና ተጠቃሚ ሁሉ ትላንት ቢኖር ኖሮ ምንኛ መልካም ነበር፡፡

በቀድሞው ጊዜ የነበሩት የየአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን አበው ለስብሰባ ተጠርተው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የሚያርፉት ቤት ተከራይተው ነበር፤ ወይም እንደሀገራችን ባህልና ሥርዐት ለብፁዓን አበው በማይስማማና በማይገባ በሆቴል ቤት ነበር፤ ለቁመተ ሥጋ ያህል ወይም ጥቂት ጥቂት የሚመገቡትም ለብፁዓን አበው የማይስማማና የማይገባ የግዥ እንጀራ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ያለፉት ብፁዓን አበው እንደተመኙት በሞተ ሥጋ የተለዩት ዓለምአቀፍ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ አሁን ባሉት የቤተ ክርስቲያን ርእስ ከፍተኛ ጥረት በመላው አህጉረ ስብከት አስተዋፅኦ ተገንብቶ ዓለም አቀፍ እንግዶችን በማስተናገድ ቤተ ክርስቲያኒቱን እጅግ አኩርቷታል፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ መኖሪያና ቢሮ በመሆንም አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ልዩ ገስት ሐውስም ተገንብቶ ቅዱስነታቸው አቻዎቻቸውን የውጭ ፓትርያርኮችን እያስተናግዱበት ነው፤ እንደ ትላንቱ ከፍተኛ ወጭ በሚጠይቁና ለአባቶች ክብር በማይስማሙ ታላላቅ ሆቴሎች ማስተናገዱ ከቀረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ከዚህም ጋራ ብፁዓን አበው ለስብሰባ ከየአህጉረ ስብከቱ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የሚያርፉበት ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት የሚበቃ ቤተ አበው በተሟላ ሁኔታ በዘመናዊ መልክ ተሠርቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ እንደ ትላንቱ ለአባቶች ክብር በማይመጥን መንደር ውስጥ ገብቶ ቤት መከራየትና ሆቴል ቤት ማደር የለም፤ እንደ ትላንቱ የግዥ እንጀራ ቢያምርም አይገኝም፤ አሁንም ዛሬ ባሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ርእስ የተለየ ጥረትና ፍላጎት በመንበረ ፓትርያርኩ ግቢ ለሚኖሩትም ሆነ ከየአህጉረ ስብከቱ ለሚመጡት ብፁዓን አበውና በግቢ ለሚኖሩት አገልጋዮች መነኮሳትም ጭምር በገዳም ሥርዐት የአንድነት ማዕድ ገበታ በነጻ ተዘርግቶላቸዋል፤ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የአባቶችን የአንድነት ገበታ በቅጡ ሲመለከቱት ሢመተ ጵጵስናው ብቻ ሳይሆን ሥርዐተ ማዕዱም ከግብጽ የመጣ ይመስላል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ተመርጠው ሢመተ ጵጵስና በሚቀበሉበትም ጊዜ ለሐዋርያዊ አገልግሎት የሚጠቀሙባቸው መኪናዎችም ሆነ ሌሎች ቁሳቁሶችን ገዝታ የምትሸልማቸው ቤተ ክርስቲያን ናት፤ መኪናዎችን መግዛት ብቻም አይደለም፤ አደጋ ሲያጋጥማቸውና በአገልግሎት ብዛት ሲዳከሙም ጋራዥ በማስገባት አሳድሳ የምትሰጣቸውም ራሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ብፁዓን አበው ሲታመሙም እስከ ውጭ አገር ድረስ በመላክ የምታሳክማቸው ቤተ ክርስቲያን ናት፤ በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበትም ጊዜ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ በክብር የምትሸኛቸውም ራሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለብፁዓን አባቶች የሚሰጠው ወርሐዊ ደመወዝ ከአባትነታቸው፣ ከአገልግሎታቸው ስፋትና ከኑሮው ወድነት ጋራ የማይመጣጠን ስለሆነ የተዘረዘረው በጎ አድራጎትና ክብካቤ ሁሉ ቢደረግላቸው የሚደሰት እንጂ የሚከፋው የለም፤ በረከትን እንጅ መርገምን ያመጣል ብሎ የሚያስብም ወገን አይገኝም፡፡

ይሁን እንጅ ቤተ ክርስቲያናችን በአስተዳደርም ሆነ በምጣኔ ሀብት ራሷን ችላ ይህ ሁሉ እየተደረገ እያለ ብፁዓን አበው በዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ በሚለዩበት ጊዜ ቀብታ የሾመቻቸውና ሲታመሙ ያስታመማቻቸው ቤተ ክርስቲያን እያለች “ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን ወራሾች እኛ ነን” እያሉ የሐሰት የውርስ ሰነድ ይዘው የሚመጡት ቤተሰብ ተብዬዎች በሚያቀርቡት አቤቱታ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ሆኑ አስተዳደሩ ፍትሕ ለመስጠት እየተቸገሩ ናቸው፤ ውርሱ ይገባናል ባዮቹ አልፈው ተርፈውም ያንኑ የሐሰት ውርስ ሰነድ ይዘው ወደየፍርድ ቤቶች በመሄድ የብፁዓን አባቶቻችንንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በማጉደፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህን ሁሉ ችግር የፈጠረውና መልኩን ለውጦ የመጣው በቅርቡ በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን አበው በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበት ጊዜ ገንዘባቸውንና ያፈሩትን ንብረት ሁሉ የሚያሳድጓቸው እጓለማውታዎችና የሚረዷቸው ችግረኞች ቤተሰቦች እንዲወርሱ በሥርዋጽ በገባው ቃል የተላለፈው ድንጋጌ ነው፡፡ ስለሆነም የብፁዓን አባቶችንም ሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ለመጠበቅ ሲባል የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ድንጋጌውን እንደገና እንዲፈትሸው ያስፈልጋል፡፡

ስለ ብፁዓን አበው ሀብትና ንብረት አወራረስ ጉዳይ የቀደሙት አበው የወሰኑት ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት ሊሠራበት ይገባል፡፡ ምናልባት በብፁዓን አባቶች ይረዱ የነበሩ እጓለማውታዎች ካሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ በቤተሰብና በሕፃናት አስተዳደግ ድርጅት ሊረዱ ይገባቸዋል፡፡ የእናትና የአባት ወይም የቤተሰብ ጉዳይ ከሆነ ግን “ዘኢኃደግ አባሁ ወእሞ፤ ወብእሲቶ ወውሉዶ፣ ኢይክል ይጸመደኒ” የሚለውን አምላካዊ ቃል መዘንጋት አያሻም፡፡

በጳጳሳት ምርጫ ጉዳይም እንደቀድሞው የካህናት እና የምእመናን ተሳትፎ ከተጨመረበት ከሞት በኋላ የሚመጣውን ጣጣ ለማስወገድ ያስችላል፡፡ ጵጵስና የሚሾመውን አባት መምረጥና መሾም የሚገባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ካህናትና ምእመናንም “አክዮስ አክዮስ ማለት ይደልዎ ይደልዎ” ብለው መምረጥና መሾም ይገባቸዋል፡፡ ይህም ከሆነ ዘንድ ሁለንተናዊ ብቃት ያለው ወይም ነውርና ነቀፋ የሌለው አባት መምረጥና መሾም ይቻላል፡፡ ከሹመት በኋላ የሚመጣውን ወቀሳና ከሰሳ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ሊሸከም አይችልም፡፡

የቀድሞዎቹ አባቶች በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበት ጊዜ አይኖራቸውም እንጅ ገንዘብና ሀብት ካላቸው የእግዚአብሔር ገንዘብ ተመልሶ ለእግዚአብሔር መሰጠት ስለአለበት ገንዘባቸውንም ሆነ ሀብታቸውን ሁሉ የሚያወርሱት ለቤተ ክርስቲያን ነበር፤ ወይም በትውልድ መንደራቸውም ሆነ በተመደቡበት ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያን በማሠራት፣ ገዳም በማስገደም፣ ት/ቤት በመክፈትና የምግባረ ሠናይ ድርጅት በማቋቋም ከአባትነት የሚጠበቅ መልካም አርኣያነት ያለው ሥራ ሠርተውበትና ዝክረ ስማቸውን ተክለውበት ያልፉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል መጥቀስ ቢያስፈልግ፣ ይህን ዓለም በመናቅ ሹመት በቃኝ ብለው በምናኔ ሕይወታቸውን በኢየሩሳሌም በርሓ የፈጸሙትን የቀድሞውን የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ መጥቀስ ብቻ ይበቃል፡፡

እኒያ እውነተኛ ብፁዕ አባት ቅድመ ሢመተ ጵጵስናም ሆነ ድኅረ ሢመተ ጵጵስና ከዕለት ምግባቸው እየቀነሱ ዕድሜ ልክ ባጠራቀሙት ገንዘብ በትውልድ ቀያቸው ዝክረ ስማቸው ለዘለዓለም ሲታወስ የሚኖርበት ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፡፡ በሚሞቱበትም ጊዜ በቁጠባ ገንዘብ ያሠሩት ቤተ ክርስቲያን እንዲገለገልበት በኑዛዜ አውርሰው በማለፋቸው ዛሬ ቤተ ክርስቲያኑ “የታዴዎስን ነፍስ ይማር” እያለ በመገልገል ላይ የሚገኘው ብፁዕነታቸው በኑዛዜ ባወረሱት ገንዘብ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን የእኒህን ብፁዕ አባት አሠረ ጽድቅ ተከትለው የሚሠሩ አባቶች የሉም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ሆኖም ብፁዓን አበው እንደ ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ያሉ አባቶች በተጓዙበት መንገድ እየተጓዙ ቢያልፉ የራሳቸውንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናቸውን ክብር ሊያስጠብቁና ዝክረ ስማቸውን ተክለው ሊያልፉ ይችላሉ፡፡

በአጠቃላይ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍ ብሎ በተጠቀሱት ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ማለትም በውርስ እና በጳጳሳት ምርጫ ላይ ትኩረት በመስጠት መክሮ እናዘክሮ ከሞት በፊትም ሆነ ከሞት በኋላ በብፁዓን አባቶች ላይ የሚከሠቱ ችግሮች እንዳይኖሩ የቀድሞውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የጠበቀ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባዋል፡፡

(መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ) by Deje Selam