Friday, October 12, 2012

የታሪካዊው እና የጥንታዊው የጋዴና ደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን

  •          ይህ ቤተክርስቲያን የሚገኜው በድቡብ ወሎ ሐገረ ስብከት በደሴ ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት ከደሴ ከተማ ወደ ወራኢሉ እና ለጋምቦ ወረዳ አቅጣጫ 64 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው ፡፡
  •          በሐገራችን ብሎም በሐገረ ስብከታችን በውጭ ሀገራት ሁሉ የሚታወቁ 3 ታላቅ አድባራት አሉ እነርሱም 1ኛ. በሐይቅ አስተዳደር  የሚገኜው ደብረ እግዚአብሔር 2ኛ. በደሴ ዙሪያ የሚገኙት መካነ ሥላሴ እና ደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ናቸው፡፡
  •     ይህ ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተው በአፄናኦድ ዘመን በከበሩ ድንጋዮች እና እነ ቅዱስ ላሊበላ ባነጹበት ተመሳሳይ ድንጋዮች የታነጸ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን በዚህ ቤተ ክርስቲያን የነበሩት  ካህናት ብዛት 1000/አንድ ሺ/ ነበሩ፡፡
  •          በዚህ ቤተ እግዚአብሔር በምላት መንፈሳዊ አገልግሎት እየተሰጠበት በገቢረ ተአምራቱ ካህናቱና ምዕመናኑ እየተጠቀሙበት ከኖረ በኋላ ክፉ ዘር የሆነ ሰይጣን የግብር ልጁን ግራኝ አህመድን በማስነሳት ህዳር 7ቀን 1524 ዓ.ም ይህን ቤተ ክርስቲያን አቃጥሎ ከካህናቱ አንዱ ሲተርፉ 999 ካህናት በአንድ ቀን ሰማዕት ሆነዋል በተለይም 5ቱ ካህናት በቤተ መቅደስ በአገልግሎት ላይ እንዳሉ በደንደሳቸው አርዶአቸዋል የእነርሱም ደም እንደጎርፍ ፈሶ የተቀላቀለበት ወንዝ ደም ባሕር ተብሎ እስካሁን ይጠራል ሲጠጡት ጨው ጨው ይላል ምክንያቱ የእነዚህ የሰማዕታት ደም ስለተቀላቀለ ነው ፡፡
  •         የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን ከቃጠሎ የተረፉ 4ትክል አምዶች እና ዙሪያውን የተቃቀፉ 13 የጥድ አጸዶች ከዚህ ደብር መካነ ሥላሴ የሚያገናኝ የተዘጋ ዋሻ ያለው ሲሆን ይህን ቦታ ሄዶ ላየው ቤተ ክርስቲያኑ ቢቃጠልም ጸጋ እግዚአብሔር ያልተለየው  ከነ ግርማው ጉብ ብሎ የሚታይ ቦታ ነው ፡፡

Wednesday, October 10, 2012

የፓትርያርክ ምርጫ እስከ ሚከናወን ድረስ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር አብረው የሚሠሩት አባላት በእርቀ ሰላሙ ጉዳይ ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋር ተወያዩ



ከጥቅምት 6-11 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ሠላሳ አንደኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ይካሔዳል፡፡ 
የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋናው ስባሰባ ደግሞ ጥቅምት 12  እንደሚጀመር እየተጠበቀ ሲሆን በአሁን ሰዓት እንዱና አንገብጋቢው አጀንዳ የፓትርያርክ ምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከውጪው ሲኖዶስ ጋር ያለውን እርቀ ሰላ በተመለከተ ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው አቡነ መልከፄዴቅ ጋር ብቻ ውይይት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ሰሞኑን የዋናው ፓትርያርክ ምርጫ እስከ ሚከናወን ድረስ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር አብረው የሚሠሩ ሰባ አባላት    ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋር ወይይት ማድረጋቸው ተነግሯል ፡፡

በውይይቱም አቡነ መርቆሬዎስ ከዚህ በፊት እንደሚገመተው ሁሉ በገዳም መኖርን እንደሚመርጡና አንድ  ጊዜ የተጣሰው ስርዓት እሳቸው በህይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ እንዲመረጥ እንደማይፈቅዱና እሳችው እስኪያርፉ አሁን እንዳለው ቤተ ክርስቲያኗ በመንበረ ፓትርያርክ እየተመራች እንድትቆይ እንደሚሹ ማስታወቃቸውን ምንጮቻችን ዘግበውልናል፡፡
ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ይጠብቅልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤  አሜን፡፡

Tuesday, October 9, 2012

“የሚያየኝን አየሁት”

የክረምት ብርድ በተለያየ ምክንያት ከቤቱ የወጣውን መንገደኛ ፊት አጨፍግጎታል፡፡ ሰጥ አርጋቸው ደርጉም ከቡድኖቹ ጋር የዕለት እንጀራውን ለመጋገር ታክሲ ውስጥ ገብቷል፡፡ እሱም ሆነ ጓደኞቹ የማውራት ፍላጎት የላቸውም፡፡ ሌሊት በእርሱ አጠራር “ግዳጅ” የሚሉት የተደራጀ የሌብነት ሥራ ሲሠሩ ስላደሩ እንቅልፍ በማጣት ዐይኖቻቸው ቀልተው አብጠዋል፡፡ የወረዛው የታክሲው መስታወት ላይ የእነሱ ትንፋሽ ተጨምሮበት በጉም ውስጥ የሚሔዱ አስመሰላቸው፡፡
“ወራጅ” አለ፤ ሰጥ አርጋቸው፤ መስታወቱን በእጁ ጠረግ ጠረግ አድርጎ ወደ ውጭ እየተመለከተ፡፡ እጁ ላይ ውፍረቱ እጅግ የሚደንቅ የወርቅ ካቴና አድርጓል፡፡ ባለታክሲው ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰበው ሕዝብ ግርግር ስለፈጠረበት አለፍ አድርጎ አወረዳቸው፡፡ ስድስት ወንዶችና ሁለት ነጠላ መስቀለኛ ያጣፉ ሴቶች እንደኮማንደር በየተራ ዱብ ዱብ አሉና ሰጥ አርጋቸውን ከበቡት፡፡ 

“ሄይ! ጊዜ አናጥፋ፤ ባለፈው ዓመት እንዳደረግነው ቶሎ ቶሎ ሒሳባችንን ዘግተን ውልቅ፡፡” ሲል፤ አንደኛዋ ሴት “አዎ በእናታችሁ መታ መታ እናድርግና ከዚህ እንጥፋ፤ ዛሬ የምንቅመው ጫት መቼም…” ስትል የቡድኑ መሪ አቋረጣትና “ዲሞትፈርሽን ይዘሻል?” አላት፡፡ በነጠላዋ ደብቃ ስለቷ የበዛ ትንሽ ምላጭ በኩራት አሳየችው፡፡ “በቃ እኔ አምና ከቆምኩበት ከመቃብር ቤቱ ጎን እቆማለሁ፡፡ ዕቃ ከበዛባችሁ እያመጣችሁ አስቀምጡ፡፡ የቡድናችንን ሕግ በየትኛውም ደቂቃ እንዳትረሱ፡፡” አላቸው፡፡ ሕጉ ከመካከላቸው አንድ ሰው ቀን ጥሎት ቢያዝ፤ ብቻውን ይወጣዋል፡፡ ስለቡድኑ መረጃ ከመስጠት ይልቅ አንገቱን ለሰይፍ ቢሰጥ ይመርጣል፡፡ 

Monday, October 8, 2012

ቅድስት አርሴማ



በአብ ስም አምኜ፣ አብን ወላዲ ብዬ፣ በወልድ ስም አምኜ፣ ወልድን ተወላዲ ብዬ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱን ሰራጺ ብዬ በማመን፤ ምንም እንኳን ለአጠይቆ አካል ሦስት ብልም፤ ዓለምን በመፍጠር፣ በማሳለፍ፣ በባህሪይና በህልውና አንድ አምላክ ብዬ በማመን የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያምንና የቅዱሳንን ሁሉ  አማላጅነት አጋዥ በማድረግ አምላክ ቅዱሳን ያቃበለኝን ያህል ስለ እምነት አርበኛዋ ቅድስት አርሴማ ትንሽ እናገራለሁ።
“በእሳት ተቃጥለው በውሃ ተቀቅለዋል፤ በሰይፍ ተመትረዋል፤ በመጋዝ ተተርትረዋል፤ በመንኩራኩር ተፈጭተዋል፤ እንደ ከብት ቆዳቸው ተገፈዋል። ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥለዋል። በዚህ ሁሉ ከሃይማኖታቸው አላፈገፈጉም።”
እንኳን ለሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ በዓለ ዕረፍቷ በዓለ ወልድ፣ እንዲሁም ተፍፃሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ መታሰቢያ በዓል  በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፤ የሰማዕቷ ምልጃ ፀሎት እና በረከቷ ከሁላችን ጋር ጸንቶ ለዘላለሙ ይኑር አሜን !!!! +++
ቅዱሳን ሰማዕታት  
ቅዱሳን ሰማዕታት ማለት “እግዚአብሔርን ካዱለጣዖት ስገዱ፤ሲባሉ እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም፤” በማለት በዓላውያን ነገስታት ፊት ቀርበው ሳያፍሩና ሳይፈሩ ስለ ፈጣሪያቸውን የመሰከሩ ናቸው። በዚህም ምክንያት ተዘርዝሮ የማያልቅ የመከራ ዓይነት ተቀብለው ለእግዚአብሔር ለፈጣሪያቸው ክብር ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ ሕይወታቸውንም የሰጡ ናቸው።
በእሳት ተቃጥለው በውሃ ተቀቅለዋል፤ በሰይፍ ተመትረዋል፤ በመጋዝ ተተርትረዋል፤ በመንኩራኩር ተፈጭተዋል፤ እንደ ከብት ቆዳቸው ተገፈዋል። ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥለዋል። በዚህ ሁሉ ከሃይማኖታቸው አላፈገፈጉም።
ለዚህ ነው፡- በዕብራውያን ፲፫፡፯ (13፡7) ላይ “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።” የተባለው።
በተጨማሪም ጌታ እራሱ በዚህ በራዕይ ፪፡፲ (2፡10) ላይም እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ “ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።”ብሏል።
በይሁዳ ፩፡፫ (1፡3) ላይም “ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።”  ይላል።

የመነኮሳት ሕይወት

ምንም እንኳን የድንግልናና የምናኔ ኑሮ ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም የምንኩስና መሥራችና አባት ቅዱስ እንጦንስ ነው፡፡ አባ እንጦንስ ግብፅ ውስጥ በምትገኝ ቆማ በምትባል ቦታ በ251 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወላጆቹ ሀብታሞችና ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከወላጆቹ ዕረፍት በኋላ የነበረውን ሀብት ለድሆች መጽውቶ መንኩሶ ብዙ ዓመት በብሕትውና ኖረ፡፡
በዚያን ጊዜ ብዙ ታምራትን ስለሠራ ሕዝቡ ግማሹ እሱን አይቶ ለማድነቅ የቀረው ደግሞ በእርሱ ጸሎት ለመፈወስ ወደነበረበት ቦታ ይጐርፍ ነበር፡፡ እርሱም በ356 ዓ.ም ዐረፈ፡፡ 

አባ ጳኩሚስ የተባለ ሌላው አባት በላይኛው ግብፅ ውስጥ ብዙ ገዳማትን በመሥራት የምንኩስናን ሕግና ሥርዓት በመወሰን ስለምንኩስና መስፋፋት ብዙ ደክሟል /290-347 ዓ.ም/፡፡ አንድ ቀን ወደ ዱር እንጨት ፍለጋ ሔዶ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸለትና እንደ አባቶቻችን ሐዋርያት የአንድነትን ማኅበር ለመሥራት መነኮሳትን እንዲሰበስብ አዘዘው፡፡ ብዙ አማኞች እየናፈቁት ማግኘት ያልቻሉትን ገዳማዊ ሕይወት ያገኙ ዘንድ ገዳም ለመመሥረት የሚስችለውንና የሚያስተዳድርበትን በነሐስ ላይ የተቀረጸ ሕግ ሰጠው፡፡ አባ ጳኩሚስም ከመልአኩ በተሰጠው ሕግ መሠረት የሚተዳደር ገዳም አቋቋመ፡፡ ይኸውም መነኮሳቱ ጠዋትና ማታ አብረው እንዲፀልዩ በአንድነት እንዲሠሩ ገቢና ወጪያቸው አንድ ላይ እንዲሆን በአንድነት እንዲመገቡ፣ ልብሳቸው አንድ አይነት እንዲሆንና እነዚህን የመሳሰሉትን ደንቦች አወጣላቸው፡፡ በዚህ መሠረት መነኮሳቱ የዕለት ምግባቸውን የሚያገኙት እየሠሩ ነበር፡፡ ከሴቶችም የምንኩስናን ሕይወት የጀመረች የአባ ጳኩሚስ እህት ማርያም ናት፡፡ 

Friday, October 5, 2012

“ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ፡፡”



እግዚአብሔር የቅዱሳንን ነፍስ ይጠብቃል ከሃጢአት እጅም ያድናቸዋ፡፡ መዝ.96፡10
እንኳን ለቅዱስ ዮሴፍ (የእመቤታችን ጠባቂ)፣ እና ለታላቁ ጸድቅ ለጻድቁ አባታችን አቡነ ሀብተማርያም ወርሃዊ ክብረ በዓል  በሰላም በጤና አደረሰን አደረሳችሁ አሜን፡፡
ቅድመ ዓለም ዘሀሎ አለም ከመፈጠሩ በፊት ለነበረ ለእግዚአብሔር አብ እና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ለለበሰ ለእግዚአብሔር ወልድ እንዲሁም ከእነሱ ባለመራቅ ለሚኖር  ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፡፡ ስለ አባቴ ጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም እንድጽፍ ስላነሳሳኸኝ  ክብርና ምስጋና ጌትነትና ውዳሴ ይገባሃል አሜን፡፡
ታላቁ ጻድቅ አቡነ ሀብተ ማርያም ከተከበሩና ህገ እግዚአብሔርን ጠብቀው በትሩፋት ከሚተጉ በንጽህናና በቅድስና ይኖሩ ከነበሩ አባታቸው ፍሬ ብሩክና እናታቸው ዮስቴና ከተባሉ በመንዝ አውራጃ ልዩ ስሙ የራዊ በተባለ ቦታ ተወለዱ፡፡ እናታቸው የምናኔ ሀሳብ ለመፈጸም በአንድ ገዳም በሄዱበት ወቅት አንድ መነኩሴ መንኩስና ላንቺ አልተፈቀደም ወደ ቤቴሽ ሂጂ ጸሎቱ ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም ሰው ሁሉ የሚማጸነው ስሙ፣ ገድሉ፣ ቱሩፋቱ ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም በአጸደ ሥጋ በአጸደ ነፍስ የሚያማልድ ምድርም ሆነ መንበረ ጸባዖትን የሚያይ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ ባሏቸው መሠረት የተወለዱና በእናታቸው ጀርባ ታዝለው ካህኑ በቤክርስቲያን “እግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ” ሲሉ በሕፃንነት አንደበታቸው “እግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ” ይሉ ነበር፡፡ ካደጉ በዃላ ትምህርታቸውን ከጥሩ ስነምግባርና ሕግን ከመጠበቅ ጠንቅቀው ከመማር ባሻገር በአባ ሳሙኤል እጅ ምንኩስናን ተቀበሉ፡፡ አቡነ መልክአ ጼዴቅ ገዳም ተነስቶ ሲሄዱ መንገድ ላይ በአንድ ዋሻ ውስጥ ለሦስት ወራት ቆይተዋል፡፡ እግዚአብሔር… “መታሰቢያህን በዚህ ዋሻ አደርገዋለሁ” ብሎ ቃልኪዳን ገባላቸው፡፡ ይህም ዋሻ የይሰበይ  አባ ሀብተ ማርያም ገዳም በመባል በሰሜን ሸዋ ሰላሌ አህጉረ ስብከት ከደብረሊባኖስ ወደ ቆላው ዝቅ ብሎ በእግር የ2 ሰዓት መንገድ ላይ ይገኛል፡፡ ገዳሙንም በስማቸው መሠረቱ፡፡ አባታችን ጽንሰታቸው ነሀሴ 26 ልደታቸው ግንቦት 26፣በዓለ ዕረፍታቸው ደግሞ ህዳር 26 ቀን ነው፡፡  “ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ፡፡” መዝሙር 111/112፡6  (“የጸድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል፡፡” መዝሙር 111/112፡6)
ሰላም ለጽንሰትከ፡-
+++++ምግባሩ የተወደደ የሆነ የጸድቁ ባህታዊ ብስራት የተጸነስክበት የእናት የዮስቴና ማህጸን በእውነት ሰላምታ ይገባል፡፡ ጻድቁ አባቴ ሆይ ሀብተማርያም እንደዮና ልጅ እንደ ጴጥሮስ የእውነት ሥራን አስተምረኝ አይነ ልቦናዬንም አብራልኝ ፍጽምት ከሆነች ትህትና ጋር ባልንጀራኤን እንደራሴ እወድ ዘንድ፡፡
ሰላም ለዝክረ ስምክ፡- በዃለኛው ዘመን የዚህን ዓለም ረሃብና ጥም የሚያስረሳና ከወይን ዘለላ ይልቅ ለሚወደድ ስም አጠራርህ ሰላምታ ይገባል፡፡ ህጻን የሆነ የማርያም ልጅ ወዳጅ ጻድቁ አባቴ አቡነ ሀብተ ማርያም ሆይ በቦታው ታርፍለት ዘንድ ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት አጥብቆ እንደ ለመነ እኔም አገልጋይ ከሀዘን ሁሉ ታድነኝና በቤቴም ታርፍ ዘንድ እለምነሃለሁ፡፡+++++

ሙሽራው ተሰወረ እውነተኛ ታሪክ



ሰሞኑን የተፈፀመ ነው ታሪኩ እንዲህ ነው ሙሽሪት እና ሙሽራው የተክሊል ስርዓታቸውን ሊፈፅሙ ከሚዜዎቻቸው ጋር ወደ ታላቁ ደብር  በጣም ብዙ ህዝብ የሚበዛበትም ቤተ ክርስቲያን  ያመራሉ  ::
በዚያም ሙሽሪት በሴቶች መግቢያ : ሙሽራው በወንዶች መግቢያ ከሚዜዎቻቸው ጋር እንዲገቡ ይሆንና በየመግቢያቸው ገብተው ስርዓተ ተክሊሉ ከሚፋፀምበት ለመገናኘት ይለያያሉ፡፡ 
ሙሽሪት መንገዱ ቀና ሆኖላት በስርዓቱ ላይ የታደሙትን እና ለቅዳሴ ለፀሎት የቆሙትን ሁሉ አላፋ ስርዓተ ተክሊሉ ከሚፋፀምበት ትደርሳለች::  ደቂቃዎች አለፉ ስርዓተ ተክሊሉን የሚፈፅሙት ካህናት ግራ ተጋቡ ሙሽሪት ብቻ ቀርባለችና::  ሙሽራን የበላው ጅብ አልጮህ አለ፡፡ ግራ የተጋቡት ካህናትም ምዕመናን መንገድ ዘግተውበት ከሆነ ብለው "እባካችሁ ሙሽራውን መንገድ አሳልፍት" እያሉ በድምጽ ማጉያ ደጋግመው መልእክታቸውን አስተላለፉ :: ከሰዉ መብዛት የተነሳ  መንገድ ተዘግቶበት ከሆነ ይመጣል የተባለው ሙሽራ ግን የውኃ ሽታ ሆነ፡፡ መቼም አያድርስ ነው የሚባለው ሙሽራው ወዴት ተሰወረ?፡፡ መቼም     "LAW አልተማርኩም" እናዳለው እኔም    "LAW አልተማርኩም"    እና በማንም አልፈርድም ግን ሁሉንም አምላክ ለበጎ አደረገው እላለህ ፡፡ እርሶ በሙሽሪት ቦታ ቢሆኑ ምን ይላሉ?

Thursday, October 4, 2012

†♥† “ተዘከር እግዚኦ ከመመሬት ንሕነ ወሰብዕሰ ከመሣዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ” †♥†



ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አባዊነ!
ከመስከረም26- ኅዳር 6 - ዘመነ-ጽጌ
“ተዘከር እግዚኦ ከመመሬት ንሕነ ወሰብሰ ከመዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ” (((መዝ.፻፪/፻፫፡፲፬-፲፭ (102/102፡14-15)))
ትርጉም፡- “አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ። ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፤” (((መዝ.፻፪/፻፫፡፲፬-፲፭ (102/102፡14-15)))
† ሁሉን ቻይ ታላቅ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ በቀንና በሌሊት የአንተን መኖር አስታውስና፣ አንተን ሁል ጊዜ በፊቴ አደርግህ ዘንድ ልቤን ምራልኝ፤ በኪሩቤል ላይ የምትኖር የቀለያትንም (ጥልቅ ባሕርንም) ጥልቀት የምትመለከት ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ፤ አቤቱ ምስጢርን ግለጽልኝ፤ ቃልህንም እናገር ዘንድ፣ ያለመሰልቸት ስለ አንተ እንድመሰክር አንተ አንደበት ሁነኝ አሜን።”

የተዘሩ አዝርዕት በቅለው የተተከሉ አትክልት ጸድቀው አብበው አፍርተው የሚታዩበት የጽጌ የልምላሜ ወቅት በመሆኑ “አሰርጎኮ ለሠማይ ወከዋክብት ወለምድርኒ በስነ ጽጌያት  ግብረ እደዊከ አዳም እግዚኦ” እያልን ጌታን የምናመሰግንበት ጊዜ ነው።
“ጽጌ” ማለት አበባ” ማለት ሲሆንዘመነ ጽጌ” ማለት የአበባ ዘመን” ማለት ነው፡፡ በሀገራችን መስከረም 25 ቀን ዘመነ ክረምት አልፎ መስከረም 26 ቀን ዘመነ ጽጌ ይጀምራል፡፡ ዘመኑ አበቦች የሚያብቡበትና ሜዳዎችንና ተራሮችን የሚያስጌጡበት ዘመን ነው፡፡ ፍሬ የተባለ ጌታን ያስገኘች እመቤታችን በአበባ ትመሰላለችና ዘመኑ የጌታንና የእመቤታችንን ነገር በአበባና በፍሬ ለመመሰል የተመቸ ነው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 ቀን ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ቀን ድረስ የጌታን እና የእመቤታችን ስደት ታስባለች፡፡ በዚህ ዘመን ቅዱስ ያሬድ እና አባ ጽጌ ድንግል ባዘጋጇቸው ድርሰቶች የጌታችን እና የእመቤታችን ስደት በማኅሌት ይታሰባል፤ ምስጋና እና ልመና ይቀርባል። ምእመናን ቤተ ክርስቲያናቸው በሠራችላቸው ሥርዓት መሠረት በፍቅርና በደስታ ይዘክሩታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስደቱን ለማሰብና በረከት ለማግኘት በርካታ ክርስቲያኖች የአዋጅ ጾም ባይሆንም በፈቃደኝነት ዘመኑን በጾም ያሳልፉታል፡፡